በአቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ የሚገኘው የአረጋውያን ተሃድሶና ልማት ማእከል የእሳት አደጋ ደረሰበት
በአደጋውም 50 ያክል የማረፊያ ክፍሎች የቃጠሎ ጉዳት ደርሶባቸዋል
በማእከሉ 1 ሺህ ገደማ ሰዎች ያሉ ሲሆን፤ በሰው ላይ የደረሰ ጉዳት እንደሌለም ታውቋል
በአዲስ አበባ ከተማ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የሚገኘው የአረጋውያን ተሃድሶና ልማት ማእከል የእሳት አደጋ ደረሰበት።
የእሳት አደጋው ዛሬ ጠዋት 3 ሰዓት ገደማ አካባቢ መከሰቱን የተቋሙ የማህበራዊ አግልግሎት ቡድን መሪ አቶ ዳዊት ቀኖ ለአል ዐይን ተናግረዋል።
እሳቱ ለአንድ ሰዓት ያክል የቆየ መሆኑን ያስታወቁት አቶ ዳዊት፤ የአዲስ አበባ ከተማ የእሳትና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የአደጋ መቆጣጠር ሰራተኞች ባደረጉት ርብርብ እሳቱ በቁጥጥር ስር መዋሉን አስታውቀዋል።
በአደጋውም 50 ያክል የማረፊያ ክፍሎች መቃጠላቸውንም ያስታወቁ ሲሆን፤ በንብረት ላይ የደረሱ ሌሎች ጉዳቶች በመጣራት ላይ ይገኛሉ።
በማእከሉ ውስጥ ወደ 1 ሺህ ደገማ ሰዎች እንደነበሩ ያስታወቁት አቶ ዳዊት በሰው ላይ የደረሰ ጉዳት እንደሌለም አስታውቀዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የአረጋውያን ተሃድሶና ልማት ማእከሉ ከአረጋውያን በተጨማሪ ከጎዳና ላይ የሚነሱ ሰዎችንም ይቀበላል።
አሁን ላይ ከ1 ሺህ በላይ ሰዎች በአረጋውያን ተሃድሶና ልማት ማእከሉ ውስጥ እንደሚገኝም ነው የማእከሉ የማህበራዊ አግልግሎት ቡድን መሪ ያስታወቁት።