በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት 113 ሚሊዮን አፍሪካውያን ሊሰደዱ ይችላሉ ተባለ
ጥናቱ በኮፕ27 ቀርቦ ውይይት የሚደረግበት ይሆናል
የአየር ንብረት ለውጡ ተጽእኖ መፍትሄ ካልተበጀለት ቁጥሩ ከዚህም ሊያሻቅብ እንደሚችል ተመላክቷል
እንደፈረንጆቹ በ2050 በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አፍሪካውያን ሊሰደዱ እንደሚችሉ በአፍሪካ አህጉር ከሚገኙ መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች በአንዱ የተደረገ አዲስ ጥናት አመላከተ፡፡
‹Money Web› እንደዘገበው ጥናቱ “ሞባይል ክላይሜት ኢንሼቲቭ አፍሪካ” በተባለ አካል የቀረበ ሲሆን “አፍሪካ ሽፍትስ ፈርስት አፍርካን ቼንጅስ” የሚል ርዕስ ሰጥቷል።
ጥናቱ እንደሚያመለክተው ለአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭ የሆኑ ብዙ የአፍሪካ ሀገራት ዜጎችን ከቤታቸው ወደ ደህና ቦታዎች የመሰደድ እድላቸው ከፍተኛ ነው ብሏል፡፡
በ2050 እስከ 113 ሚሊዮን ሰዎች የፍልሰት ስጋት አለባቸውም ነው ያለው ጥናቱ፡፡
የአየር ንብረት ለውጡ ተጽእኖ መፍትሄ ካልተበጀለት በዚህ ከቀጠለ ለጎርፍና አውሎ ንፋስ ተጋላጭ ከሆኑ ሀገራት የሚፈልሱ ሰዎች ቁጥር ከዚህም ሊያሻቅብ እንደሚችል ጥናቱ አሳስቧል፡፡
ጥናቱ በአሁኑ ወቅት በግብጽ ሻርም ኤል ከተማ እየተካሄደ ባለው የኮፕ-27 የአየር ንብረት ጉበዔ ላይ ቀርቦ ውይይት ይደረግበታል ተብሏል፡፡
የተመድ ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ለዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ጉባኤ ለተሰበሰቡ መሪዎች ዓለም “ወደ አየር ንብረት ገሃነም በሚወስደው ጎዳና ላይ ናት” ሲሉ ማስጠንቀቃቸው አይዘነጋም፡፡
የዘንድሮው የተመድ የአየር ንብረት ጉባኤ (COP27) የሙቀት መጠን መጨመርን ለመከላከል ጊዜው እያለቀ ነው የሚል ስጋትም ነበር ያነሱት ወና ጸሃፊው፡፡
ዋና ጸሀፊው የበለጸጉ ሀገራት ልቀትን ለማስወገድ በሀብታምና በድሃ ሀገራት መካከል አዲስ ስምምነት እንዲደረግም ጥሪ አቅርበዋል።