በአፍሪካ ቀንድ በድርቅ ምክንያት “22 ሚሊዮን ሰዎች ለረሃብ አደጋ ሊጋለጡ እንደሚችሉ” ተመድ አስጠነቀቀ
የዓለም የምግብ ፕሮግራም፤ በሶማሊያ ብቻ 15 ሚሊዮን ህዝብ ለጠና ረሃብ መጋለጡ አስታውቋል
ደብሊውኤፍፒ የረሃብ አደጋውን ለማስቆም “በቀጣዮቹ ስድስት ወራት ብቻ 418 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ያስፈልጋል” ብሏል
በድርቅ በተጠቃው የአፍሪካ ቀንድ ለረሃብ ሊጋለጡ የሚችሉ ሰዎች ቁጥር ወደ 22 ሚሊዮን ከፍ ማለቱ የተባበሩት መንግስታት የዓለም የምግብ ፕሮግራም (ደብሊውኤፍፒ) አስታወቀ።
ደብሊውኤፍፒ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው ለረሃብ የተጋለጡ ሰዎች ቁጥር መጨመር በኬንያ፣ ሶማሊያ እና ኢትዮጵያ የተስተዋለውና ለዓመታት የዘለቀው በቂ ያልሆነ የዝናብ መጠን ያስከተለው ድርቅ መሆኑ በምክንያትነት አስቀምጧል፡፡
የተከሰተው ድርቅ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የቤት እንስሳትን ገድለዋል፣እህል አውድመዋል እንዲሁም 1ነጥብ 1 ሚሊዮን ሰዎች ምግብና ውሃ ፍለጋ ከቤት ንብረታቸው እንዲፈናቀሉ አድርጓልም ብሏል የድርጅቱ መግለጫ፡፡
የዓለም የምግብ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ዴቪድ ቤስሊ "በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ ያለው መጠነ ሰፊ የረሃብ አደጋን ለመከላከል ዓለም አሁን እርምጃ መውሰድ አለበት" ብለዋል።
“ይህ የድርቅ አደጋ አሁንም ፍጻሜ የለውም፣ ስለዚህም ህይወትን ለመታደግ እና ሰዎች ወደ አስከፊ የረሃብ ደረጃ መግባታቸውን ለማስቆም የሚያስፈልጉትን ሀብቶች ማግኘት አለብን” ሲሉም ተናግረዋል ።
ደብሊውኤፍፒ እንደፈረንጆቹ በ2022 መጀመሪያ ላይ በሶስቱ ሀገራት 13 ሚሊዮን ሰዎች ለረሃብ ሊጋለጡ እንሚችሉና ለጋሾች ቦርሳቸውን እንዲከፍቱ መማጸናቸው አይዘነጋም፡፡
ይሁን እንጅ የሚያስፈልገው የፋይናንስ የድጋፍ መጠን ባለመገኘቱ ፤ የተከተው ድርቅ ያስከተለው የረሃብ አደጋ አሁን ላይ ወደ ከፋ ደረጃ እየደረሰ መሆኑ ድርጅቱ አሳስቧል፡፡
በዚህም መሰረት “የፊታችን መስከረም 22 ሚሊዮን ሰዎች ለረሃብ አደጋ ሊጋለጡ ይችላሉ” ሲል አስጠንቅቋል፡፡
ቀጣዩ የዝናብ ወቅት ካልተሳካና ቁጥሩ እየጨመረ ሄዶ በጣም ተጋላጭ የሆኑ ሰዎች ሰብዓዊ እርዳታ ካላገኙ የረሃብ መጠኑ እየተባበሰ እንዲሚሄደም የድርጅቱ መግለጫ አመላክቷል፡፡
በተለይም በሶማሊያ “ወደ ግማሽ የሚጠጋው 15 ሚሊዮን ህዝብ በጠና የተራበ ነው” ያለው የደብሊውኤፍፒ መግለጫ፤ የተጋረጠውን ችግር ለመግታት እስከ 2023 ድረስ አስፈላጊውን ድጋፍ ሊደረግ ይገባል ሲልም ጠይቋል፡፡
“በቀጣዮቹ ስድስት ወራት ውስጥ ብቻ 418 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ያስፈልጋል”ም ብሏል ደብሊውኤፍፒ፡፡