የ115 አመት ልደታቸውን ያከበሩት አዛውንት የረጅም እድሜያቸውን ሚስጢር ይናገራሉ
ታይታኒክ ስትሰምጥ የ4 አመት ልጅ የነበሩት ብራዚላዊት ሄሌና ፔሬራ ባቄላ ከማዕዳቸው አይጠፋም

ሰላማዊ እንቅልፍ እና የአካል ብቃት እንቅስቅሴም ለረጅም እድሜያቸው ምክንያት መሆናቸውን ያነሳሉ
የ115 አመቷ ብራዚላዊት አዛውንት የረጅም እድሜያቸው ሚስጢር ከባቄላ ጋር የተያያዘ አመጋገብ መሆኑን ተናግረዋል።
ሄላ ፔሬራ ዶሳንቶስ የተሰኙት አዛውንት ከ15 የልጅ ልጅ ልጆቻቸው ጋር በቅርቡ ልደታቸውን አክብረዋል።
በፈረንጆቹ 1908 የተወለዱት ሄሌና ታይታኒክ ስትሰምጥ የአራት አመት ልጅ ነበሩ፤ ስድስተኛ አመታቸው ላይም አንደኛው የአለም ጦርነት ተጀምሯል።
ለ11 አስርት አመታት በጤና እና በጥንካሬ እንድቆይ ካደረጉኝ ጉዳዮች ውስጥ አመጋገቤ ከባቄላ ጋር የተያያዘ መሆኑ ቀዳሚው ይመስለኛል ይላሉ ሄሌና።
“ባቄላ ስጋን ይተካል” በሚል የምንሰማው መረጃ በሀገረ ብራዚልም ስለመኖሩ ግን የሚረር ዘገባ አልተጠቀሰም።
አዛውንቷ ከአመጋገባቸው ባሻገር በቂ እንቅልፍ መተኛት፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግና ደስተኛ መሆን ለረጅም እድሜያቸው አስተዋጽኦ ያደረጉ ወሳኝ ጉዳዮች መሆናቸውን ያክላሉ።
ከሳኦ ፖሎ በስተደቡብ በምትገኘው ሪዮ ዳስ ፔድራስ ነዋሪ የሆኑት ሄላና አሁንም ድረስ ጥንካሬያቸው አልተለያቸውም የሚሉት ልጆቻቸው፥ የሌሎችን ድጋፍ ያለመፈለግ እና ለገበያ የመውጣት ልማዳቸው እንዳልለቀቃቸው ይናገራሉ።
በ26 አመታቸው ትዳር የመሰረቱት ሄሊና በፈረንጆቹ 2004 በ103 አመታቸው ከተለዩዋቸው ባላቸው ስድስት ልጆችን ወልደዋል።
ልጆቻቸው እንደሳቸው ረጅም እድሜ ያልቆዩላቸው ሄሊና 10 የልጅ ልጅ እና 15 የል ልጅ ልጅ ለማየት ታድለዋል።