ለ50 አመታት በውሃና ለስላሳ መጠጦች ብቻ ኖሬያለሁ የሚሉት የ75 አመት አዛውንት
ቬትናማዊት አዛውንት ከ1970 ወዲህ ምንም አይነት ምግብ በአፌ አልዞረም ባይ ናቸው
የጤና ባለሙያዎች ግን ለስላሳ መጠጦችን ማዘውተር ለተለያዩ ህመሞች እንደሚዳርግ ይገልጻሉ
በደቡብ ምስራቅ እስያዋ ሀገር ቬትናም በ50 አመታት ውስጥ ምንም ምግብ ሳልመገብ በውሃ እና ለስላሳ መጠጦች ብቻ መኖር ችያለሁ የሚሉት አዛውንት ትኩረት ስበዋል።
ካንግ ቢንህ በተሰኘችው ግዛት የሚኖሩት ቡይ ቲ ሎይ እድሜያቸው 75 አመት ቢደርስም በጥሩ አቋም ላይ ይገኛሉ።
አዛውንቷ በልጅነታቸው በ1963 ከጓደኞቻቸው ጋር በጦርነት የተገዱ ወታደሮችን ለመርዳት ተራራ ሲወጡ በመብረቅ መመታታቸው ከምግብ ጋር አጣልቷቸው መቅረቱን ይናገራሉ።
በአደጋው ራሳቸውን ስተው የቆዩት ቡይ ቲ ሊዩ ምግብ አለመገብም ብለው ማስቸገራቸውን ተከትሎ ጣፋጭ መጠጦችን ይሰጧቸው ጀመር።
ከአመታት በኋላ በተወሰነ በጓደኞቻቸውና ወዳጆቻቸው ጫና ፍራፍሬ እና የተወሰኑ ጠጣር ምግቦችን ቢጀምሩም ከፈረንጆቹ 1970 ጀምሮ ግን ከናካቴው ምግብ አያሳየኝ ማለታቸውን ያስታውሳሉ።
የምግብ ማቀዝቀዣቸውን በለስላሳ መጠጦች እና በውሃ የሞሉት አዛውንት ከምግብ ከተለያየሁ ከግማሽ ክፍለዘመን በላይ ተቆጥረዋል ሲሉም ነው የተደመጡት።
ቬትናማዊቷ እናት ለልጆቻቸው ምግብ እየሰሩ እንኳን አንድም ቀን ቀምሰውት እንደማያውቁ ይናገራሉ።
ልጆቻቸው አድገው ከቤት ከወጡ በኋላም ምግብ ማብሰያ ክፍላቸው በሸረሪት ድር ተወሯል ይላል ኦዲቲ ሴንትራል በዘገባው።
የ75 አመቷ አዛውንት ያልተለመደ አመጋገብ በርግጥም እውነት ስለመሆኑ ማረጋገጥ ቢከብድም ለስላሳ መጠጦች በፍጥነት ሃይል መስጠትና ህይወት የማስቀጠል አቅም እንዳላቸው የህክምና ባለሙያዎች ይገልጻሉ።
ይሁን እንጂ ለስላሳ መጠጦችን ማዘውተር እንደ የስኳር በሽታ፣ ከልክ ያለፈ ውፍረት፣ የደም ግፊት እና የልብ ህመም ሊዳርጉ እንደሚችሉ ነው የሚነገረው።
ቬትናም እንደ ቡይ ቲ ሎይ ሁሉ የመገናኛ ብዙሃንን ትኩረት የሚስቡ ጉዳዮችን እንካችሁ ማለትን አስለምዳለች።
በዚሁ አመት ታይ ጎክ የተባለ የ80 አመት አዛውንት ለ60 አመት እንቅልፍ አልተኛሁም ማለታቸውን መዘገባችን ይታወሳል።