118 ሀገራት የታዳሽ ሃይል ልማታቸውን በሶስት እጥፍ ለማሳደግ ተስማሙ
ሀገራቱ ከጸሃይ፣ ከንፋስ እና ከውሃ የሚገኘውን ሃይል በ2030 ወደ 11 ሺህ ጊጋዋት ከፍ ለማድረግ ነው የተስማሙት
በዱባይ እየተካሄደ የሚገኘው የአለም አየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ የተለያዩ ስምምነቶች እየተፈረሙበት ነው
118 ሀገራት የታዳሽ ሃይል ልማት ላይ በትብብር መስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት በዱባይ ተፈራርመዋል።
አስገዳጅነት አይኖረውም የተባለው ስምምነት በ2030 ከታዳሽ የሃይል ምንጮች የሚገኘውን ሃይል አሁን ካለበት በሶስት እጥፍ ለመጨመር የሚያስችል ነው።
ሀገራቱ ከጸሃይ፣ ንፋስ እና ውሃ የሚገኘውን የኤሌክትሪክ ሃይል ወደ 11 ሺህ ጊጋዋት ከፍ ለማድረግ ነው ቃል የገቡት።
እቅዱን ለማሳካት የሀገራት ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ መግባቱን የኮፕ28 ፕሬዝዳንት ዶክተር ሱልጣን አል ጀበር ገልጸዋል።
118ቱ ሀገራት የሃይል አጠቃቀማቸውን ለማዘመን እና ብክነትን ለመቀነስ መስማማታቸውም በዱባይ በተፈረመው የቃልኪዳን ሰነድ ላይ ሰፍሯል።
ከአለማችን የከባቢ አየር ብክለት 80 በመቶ ድርሻ ያላቸው የቡድን 7 እና 20 አባል ሀገራትም ለዚህ ስምምነት ድጋፋቸውን መስጠታቸው ተገልጿል።
የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ቮን ደር ላይን ስምምነቱ በታዳሽ ሃይል ልማት ላይ ለተሰማሩ አልሚዎች “ትልቅ ብስራት” ነው ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት በአለማቀፍ ደረጃ ከታዳሽ የሃይል ምንጮች የሚገኘው ሃይል 3 ሺህ 400 ጊጋዋት ብቻ መሆኑንም ነው ያብራሩት።
የአለማቀፉ የታዳሽ ሃይል ኤጀንሲ መረጃ እንደሚያሳየው በ2022 መጨረሻ የታዳሽ ሃይል ምንጮች ያስገኙት ሃይል 3 ሺህ 372 ጊጋዋት ነው፤ ከዚህም ውስጥ 37 ከመቶው ከውሃ፤ 31 ከመቶው ደግሞ ከጸሃይ የተገኘ ነው።