ሼክ ሞሃመድ ቢን ዛይድ አረብ ኢምሬትስ ለአየር ንብረት መፍትሄዎች የ30 ቢሊዮን ዶላር ፈንድ ማቋቋሟን አስታወቁ
የ28ኛው የመንግስታቱ ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ (ኮፕ28) በዱባይ እየተካሄደ ነው
የአየር ንብረት መፍትሄ ፈንድ የአየር ንብረት ፋይናንስ ክፍተትን ለመሙላት እንደሚውል አስታውቀዋል
የአረብ ኢምሬትስ ፕሬዝዳንት ሼክ ሞሃመድ ቢን ዛይድ ሀገራቸው ለአየር ንብረት ለውጥ መፍትሄዎች የ30 ቢሊዮን ዶላር ፈንድ ማቋቋሟን አስታወቁ።
ሼክ ሞሃመድ ቢን ዛይድ ይህንን ያሉት 28ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ (ኮፕ28) በመሪዎች ደረጃ ሲከፈት ባደረጉት ንግግር ነው።
በዚሁ ወቅትም ሼክ ሞሃመድ ቢን ዛይድ አል ናህንያን ለአየር ንብረት መፍትሄዎች ፈንድ የተቋቋመው የአየር ንብረት ፋይናንስ ክፍተቱን ለመሙላትና እና ገንዘቡ በተገቢው መልኩ ተደራሽነቱን ለማመቻቸት ነው ብለዋል።
ሼክ ሞሃመድ ቢን ዛይድ አክለውም የገንዘብ እጥረት በዓለም አቀር የአየር ንብረት ለውጥ እርምጃዎች ላይ ትልቁ እንቅፋት መሆኑንም አብራርተዋል።
አረብ ኢምሬትስ በታዳሽ እና ንጹህ የኃይል ምንጭ መጠቅማ ላይ ትኩረት እንደምታደርግም ፕሬዝዳንቱ አስታውቀዋል።
በዚሁ ወቅትም ሼክ ሞሃመድ ቢን ዛይድ አረብ ኢምሬትስ በቀጣይ 7 ዓመታት ውስጥ ለአየር ንብረት ለውጥ እርምጃ በታዳሽ እና ንጹህ የኃይል ምንጭ ዘርፍ ተጨማሪ 130 ቢሊየን ዶለር ኢንቨስት እንደምታደርግም አስታውቀዋል።
የተመድ ዋና ጸሃፊው በኮፕ28 ጉባኤ ባደረጉት ንግግር፥ የአየር ንብረት ለውጥ ከአንታርቲካ እስከ ኔፓል ጉልህ ተጽዕኖውን እያሳየ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
“ከፍተኛው የአለም የሙቀት መጠን በዚህ አመት ተመዝግቧል፤ ወደ ከባቢ አየር የተለቀቀው ካርበንም ከፍተኛው ነው፤ ድርቅና ጎርፉም እየተባባሰ ሄዷል” ያሉት አንቶኒዮ ጉቴሬዝ፥ በፓሪስ የተደረሰውን ስምምነት መፈጸም አለመቻሉ ፈተናውን እያከበደው መሄዱን አብራርተዋል።
በመሪዎች ደረጃ የሚካሄደው 28ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ዛሬ መካሄድ የጀመረ ሲሆን፤ እስከ ነገ ይቀጥላል።
በዚሁ የመሪዎች ጉባዔ ላይ የ137 ሀገራት እና መንግስታት መሪዎች ንግግር እንደሚያድርጉም የወጣው ምርሃ ግብር ያመለክታል።