የአፍሪካ ተደራዳሪ ቡድን የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳት ፈንድ መቋቋሙን አወደሰ
ለአየር ንብረት ለውጥ ጉዳት ፈንድ በሁለት ቀናት ውስጥ 400 ሚሊዮን ዶላር ተዋጥቷል
ፈንዱ በዓመት 100 ቢሊዮን ዶላር ከዓለም ሀገራት እና ተቋማት የመሰብሰብ ውጥን ይዟል
የአፍሪካ ተደራዳሪ ቡድን የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳት ፈንድ መቋቋሙን አወደሰ።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በየዓመቱ በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ የዓለም ሀገራት፣ የአየር ንብረት ለውጥ ባለሙያዎችን እና ሌሎች የሚመለከታቸውን አካላት ጋር ይመክራል፡፡
ይህ ጉባኤ በተመድ አባል ሀገራት እየተዟዟረ በየዓመቱ የሚካሄድ ሲሆን የዘንድሮው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ከዛሬ ጀምሮ በተባበሩት አረብ ኢምሬት አስተናጋጅነት በዱባይ በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡
በዚህ ጉባኤ ላይ እየተሳተፉ ያሉት 54ቱን የአፍሪካ ሀገራት ወክለው ሲደራደሩ የነበረው ቡድን እንዳለው በኮፕ28 ጉባኤ ላይ የተወሰነው ውሳኔ እንዳስደሰተው አስታውቋል።
የበለጸጉ ሀገራት በኢንዱስትሪዎቻቸው በሚለቁት በካይ ጋዝ ምክንያት ታዳጊ ሀገራት ላይ በሚደርስ የአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ያልተገባ ጉዳት እያስተናገዱ እንደሆነ ተገልጿል።
የቡድኑ መሪ እንዳሉት የኮፕ28 ፕሬዝዳንት ዶክተር ሱልጣን ቢን አህመድ አል ጃቢር የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳት ፈንድ እንዲቋቋም ታሪካዊ አመራር መስጠታቸውንም ቡድኑ አስታውቋል።
አረብ ኢምሬት ለዚህ ፈንድ 100 ሚሊዮን ዶላር ስታዋጣ፣ አሜሪካ 17.5 ሚሊዮን ዶላር፣ ብሪታንያ 40 ሚሊዮን ፓውንድ ስተርሊንግ፣ ጃፓን 10 ሚሊዮን ዶላር፣ የአውሮፓ ህብረት ደግሞ 145 ሚሊዮን ዩሮ በድምሩ ለፈንዱ በሁለት ቀናት ውስጥ 400 ሚሊዮን ዶላር መዋጣቱ ተገልጿል።