የጣልያን ጠቅላይ ሚንስትር ጆርጂያ ሜሎኒ በዱባይ እየተካሄደ ባለው የተመድ አየር ንብረት ጉባኤ ላይ በመሳተፍ ላይ ናቸው
ጣልያን ለአፍሪካ አራት ቢሊዮን ዩሮ እንደምትሰጥ ገለጸች።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በየዓመቱ በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ የዓለም ሀገራት፣ የአየር ንብረት ለውጥ ባለሙያዎችን እና ሌሎች የሚመለከታቸውን አካላት ጋር ይመክራል፡፡
ይህ ጉባኤ በተመድ አባል ሀገራት እየተዟዟረ በየዓመቱ የሚካሄድ ሲሆን የዘንድሮው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ከዛሬ ጀምሮ በተባበሩት አረብ ኢምሬት አስተናጋጅነት በዱባይ በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡
በዚህ ጉባኤ ላይ እየተሳተፉ የሚገኙት የጣልያን ጠቅላይ ሚንስትር ጆርጂያ ሜሎኒ እንዳሉት አፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥን እንድትከላከል አራት ቢሊዮን ዩሮ እንደምትሰጥ ተናግረዋል።
አፍሪካ የበጎ አድራጎት ወይም እርዳታ አያስፈልጋትም ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሯ አህጉሪቱ ባላት ሀብት በዓለም ላይ ተወዳድሮ ውጤታማ እንዲሆን ማገዝ ያስፈልጋልም ብለዋል።
ጠቅላይ ሚንስትር ሜሎኒ አክለውም አውሮፓ ቀስ በቀስ የድንጋይ ከሰል የሀይል አማራጭን በመተው ላይ መሆኗንም ተናግረዋል።
ሀገራቸው ጣልያንም በ2050 ሙሉ ለሙሉ ታዳሽ ሀይልን ትጠቀማለች ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሯ በ2030 ደግሞ ከታዳሽ ሀይል እሚገኘውን ሀይል ድርሻ 55 በመቶ የማድረስ እቅድ እንዳላትም ገልጸዋል።