ከአንድ ወር በኋላ ሊካሄድ ታስቦ የነበረው የጣና ፎረም ወደ ሚያዝያ ተራዘመ
የጣና ፎረም በየዓመቱ በባህርዳር የሚካሄድ አህጉር አቀፍ የሰላምና ደህንነት ጉባኤ ነው
ጉባኤው ለምን እንደተራዘመ እስካን በይፋ አልተገለጸም
ከአንድ ወር በኋላ ሊካሄድ ታስቦ የነበረው የጣና ፎረም ወደ ሚያዝያ ተራዘመ፡፡
ትኩረቱን በሰላምና ደህንነት ዙሪያ በማድረግ በየዓመቱ የሚካሄደው ጣኛ ፎረም ከአንድ ወር በኋላ እንደሚካሄድ እቅድ ተይዞለት ነበር፡፡
ከ13 ዓመት በፊት በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የተመሰረተው ይህ አህጉር አቀፍ የሰላምና ደህንነት ተቋም የግጭት አፈታት፣ ዘላቂ ሰላም ማስጠበቅ እና የተለያዩ ጥናቶች ሲቀርቡበት ቆይቷል፡፡
የዘንድሮው እና 11ኛው ጣና ፎረም ከጥቅምት 2 እስከ 4 ቀን 2016 ዓ.ም በባህርዳር እንደሚካሄድ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም መራዘሙን ድርጅቱ በትዊትር ገጹ ላይ አስታውቋል፡፡
ጣና ፎረም ላይ የአሜሪካውን ከፍተኛ ዲፕሎማት ያበሳጨው የአፍሪካ ምሁራን ጥያቄ ምንድን ነው..?
ይሁንና ጉባኤው ለምን እንደተራዘመ በይፋ ያልተገለጸ ሲሆን የፊታችን ሚያዝያ እንደሚካሄድ ገልጿል፡፡
ድርጅቱ ባወጣው መግለጫ ጉባኤው ወደ ሚያዝያ የተራዘመው ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከፎረሙ የቦርድ አመራሮች እና ከሚመለከታቸው ሌሎች አካላት ጋር ውይይት ከተደረገ በኋላ መሆኑን አስታውቋል፡፡
በአማራ ክልል በተከሰተው ጦርነት ምክንያት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባሳለፍነው ሀምሌ ለስድስት ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መጣሉ ይታወሳል፡፡
በክልሉ ሁሉም ቦታዎች የኢንተርኔት አገልግሎት ከተቋረጠ ሁለተኛ ወሩን የያዘ ሲሆን ካሳለፍነው ሳምንት ጀምሮም በተወሰኑ የክልሉ ቦታዎች የሞባይል ኔትወርክ ተቋርጧል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ የአፍሪካ ህብረት፣ ኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንን ጨምሮ አሜሪካ፣ የአውሮፓ ህብረት እና ሌሎች ሀገራት በኢትዮጵያ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ያሉ የሰብዓዊ መብት ሁኔታዎች እንዳሰሰቧቸው ጉዳዩን አስመልክተው ባወጧቸው መግለጫዎች ላይ ጠቅሰዋል፡፡