ጣና ፎረም ላይ የአሜሪካውን ከፍተኛ ዲፕሎማት ያበሳጨው የአፍሪካ ምሁራን ጥያቄ ምንድን ነው..?
ከምባሳደር ማይክ ሀመር ለቀረበላቸው ጥያቄ ስሜት በተቀላቀለበትና ሀገራቸውን በሚከላከል መንገድ ምላሽ ሰጥተዋል
ምሁራኑ ካቀረቧቸው ጥያቄዎች መካከልም አፍሪካ የራሷን ችግር በራሷ እንድትፈታ ለምን አትተዋትም? የሚል ይገኝበታል
በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ስር ያለው የሰላምና ደህንነት ኢንስቲትዪት የተዘጋጀው 10ኛው የጣና ፎረም በባህርዳር ተካሂዷል።
በአፍሪካ ሰላምና ደህንነት ላይ ባተኮረው በዚህ ጉባኤ ላይ ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ የሰላም፣ ፖለቲካ እና ደህንነት ምሁራን፣ መሪዎች እና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች ተሳትፈውበታል።
የዚህ ጉባኤ አንድ አካል የሆነው "የአፍሪካ የሰላምና ደህንነት ስነ ምህዳር እና ምላሾች" በሚል ርዕስ ዙሪያ በተደረገው የፓናል ውይይት ላይ አፍሪካዊያን ምሁራን ከአውሮፓ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ አምባሳደር አቴ ዌበር (ዶ/ር) ፣ በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ አምባሳደር ማይክ ሀመር፣ የተመድ የአፍሪካ ቀንድ አምባሳደርሀና ቴተህ፣ የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ እና ሌሎችም ተገኝተዋል።
በዚህ ወቅት ታዋቂው ኬኒያዊው የህግ እና ፖለቲካ ተንታኙ ፕሮፌሰር ፓትሪክ ሉሙምባን ጨምሮ ሌሎችም አፍሪካዊያን ምሁራን ለአምባሳደር ሀመር ጥያቄ አቅርበዋል።
ምሁራኑ ለአምባሳደር ማይክ ሐመር ካቀረቧቸው ጥያቄዎች መካከልም አፍሪካ የራሷን ችግር በራሷ እንድትፈታ ለምን አትተዋትም? አሜሪካ በአፍሪካ የውስጥ ጉዳዮች ጣልቃ እየገባች ነው፤ እንዲሁም ቻይና ለአፍሪካ ከአሜሪካ በተሻለ መንገድ እየሰራች ነው እና ሌሎችም ተያያዥ ጉዳዮችን አንስተዋል።
በውይይቱ ባህርዳርን እና አካባቢዋ ያላትን ውበት በማድነቅ የጀመሩት አምባሳደር ማይክ ሀመር በሰሜን ኢትዮጵያ ባሉ አካባቢዎች በርካታ ንጹሀን ዜጎች በጦርነቱ እየተጎዱ እና ህይወታቸውን እያጡ በመሆኑ ጦርነቱ ሊያበቃ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ከአፍሪካ ምሁራን ለተነሳላቸው ጥያቄ ስሜት በተቀላቀለበት መንገድ ሀገራቸውን በሚከላከል መንገድ ምላሽ ሰጥተዋል።
አፍሪካ ችግሯን በራሷ እንድትፈታ አሜሪካ ለምን አትተወንም? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄም "አፍሪካ በራሷ ችግሯን መፍታት ትችላለች?" ሲሉ ጥያቄ በመጠየቅ ምላሽ የሰጡት አምባሳደር ማይክ ሀመር " እንደዛ ማድረግ እምትችል አይመስለኝም" ሲሉም አክለዋል።
" እኔ ባህርዳር የተገኘሁት ምን ማድረግ እንዳለባችሁ ለመንገር አይደለም። አፍሪካም ሆነች አሜሪካ ችግራቸውን ለመፍታት በጋራ መስራት ግን አለባቸው ብለዋል" ሲሉም አምባሳደሩ ተናግረዋል።
አምባሳደር ማይክ ሀመር አክለውም " በአፍሪካ እንደ አሜሪካ ብዙ ገንዘብ ኢንቨስት ያደረገ ሀገር ወይም ተቋም የለም፣ የአፍሪካዊያንን ህይወት በመታደግ ከአሜሪካ በላይ የሰራ ሀገር የለም፣ ፍጹም ላንሆን እንችላለን ፣ አሜሪካ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለባትን ሀላፊነት ታውቃለች ነገር ግን በብዙ መንገድ ለአፍሪካ ድጋፍ እያደረግን እንገኛለን " በሚል ከምሁራኑ ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል።
የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ በበኩላቸው "አሜሪካ ለአፍሪካ ድጋፍ እያደረገች ቢሆንም አፍሪካ ራሷን በምትችልበት መንገድ ድጋፍ እያደረገች አይደለም" ሲሉ ለአምባሳደር ማይክ ሐመር ምላሽ ሰጥተዋል።
አሜሪካ በተለይም ስንዴ እና መሰል የሰብዓዊ እርዳታዎችን ለአፍሪካ ድጋፍ ብታደርግም አፍሪካ ከተረጅነት እንድትወጣ የሚያደርግ ፖሊሲ የላትም ሲሉም ዋሸንግተንን ተችተዋል።