የኢትዮጵያ መንግስት በጉዳዩ ላይ እስካሁን ያለው ነገር የለም
የአሜሪካ መንግስት ለፍትህ ቢሮውና ለውጭ ጉዳይ ሚንስቴር በኮንትራት ተቀጥሮ ይሰራ የነበረውን ግለሰብ በስለላ ጠርጥሮ አስሯል።
አቃቢያን ህጎች ግለሰቡ ሚስጥራዊ መረጃዎችን ለኢትዮጵያ በማቀበል እንደጠረጠሩት አስታውቀዋል።
አብርሀም ተክሉ ለማ የተባለው ግለሰብ ሦስት ክሶች ቀርበውበታል ተብሏል።
የሀገሪቱ ፍትህ ቢሮ የብሄራዊ መከላከያ መረጃዎችን ለሌላ ሀገር በማስተላለፍ፣ ለውጭ ሀገር የመከላከያ መረጃዎችን ለማስተላለፍ በማሴር እና ጥብቅ የመከላከያ መረጃዎችን በመያዝ ወንጀሎች ክስ እንዳቀረበ ገልጿል።
ሮይተርስ እንደዘገበው ተጠርጣሪው ከታህሳስ 2022 እስከ ነሀሴ 2023 ድረስ ከደህንነት ሪፖርቶች ሚስጥራዊ መረጃዎችን ቀድቷል ተብሏል።
አቃቢያን ህጎች በቀጥታ የኢትዮጵያን ስም ባያነሱም፤ ግለሰቡ ለትውልድ ሀገሩ፣ ቀድሞ ዜጋ ለሆነበትና ቤተሰቦቹ ለሚኖሩበት ሀገር ሰልሏል ብለዋል።
ፍትህ ቢሮ በተጨማሪም ግለሰቡን "ትውልደ ኢትዮጵያዊ የአሜሪካ ዜጋ" ሲል ጠርቶታል።
በስለላ ወንጀል የተጠረጠረው አብርሀም ተክሉ ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ ከእድሜ ልክ እስራት እስከ የሞት ፍርድ ይጠብቀዋል ተብሏል።
የኢትዮጵያ መንግስት በጉዳዩ ላይ እስካሁን ያለው ነገር የለም።