ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ የስደተኛ ሰራተኞችን ደህንነት ለመጠበቅ ተስማሙ
ስምምነቱ የስደተኛ ሰራተኞችን ደህንነት ለማስጠበቅ ያለመ እንደሆነ ተገልጿል
ኢትዮጵያ ተመሳሳይ ስምምነቶችን ከአፍሪካ ቀንድ እና አረብ ሀገራት ጋር ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ነው ተብሏል
ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ የስደተኛ ሰራተኞችን ደህንነት ለመጠበቅ ተስማሙ።
ሁለቱ የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት በሀገሮቻቸው ያሉ ስደተኛ ሰራተኞችን ደህንነት ማስጠበቅ ዓላማው ያደረገ ስምምነት በአዲስ አበባ ተፈራርመዋል።
በዓለም አቀፉ የሰራተኞች ድርጅት ወይም አይኤልኦ አስተባባሪነት የተፈረመው ይህ ስምምነት በሰራተኖች ደህንነት ዙሪያ ትብብር፣ ጥበቃ እና ሌሎች ስራዎችን በጋራ መስራት ያስችላል ተብሏል።
ስምምነቱን የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ ከሶማሊያ አቻቸው ኦማር ፋሩክ ኦስማን እና በአይኤልኦ የአፍሪካ ቀንድ አስተባባሪ አሌክሲዮ ሙሲንዶ ተፈራርመዋል።
አቶ ካሳሁን በዚህ ጊዜ እንዳሉት የሁለትዮሽ ስምምነቱ ወደ ሶማሊያ የገቡ ኢትዮጵያዊያን ሰራተኞች ደህንነት እንዲጠበቅ የሚያደርግ ነው ብለዋል።
በቀጣይም ወደ ምስራቅ አፍሪካ እና መካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ያቀኑ ኢትዮጵያዊያን ስደተኛ ሰራተኞች ደህንነት ለማስጠበቅ ተመሳሳይ ስምምነቶችን ለመፈራረም ውይይት እያደረጉ መሆኑንም አቶ ካሳሁን በስምምነቱ ላይ ተናግረዋል።
በቅርቡም በደቡብ ሱዳን ያሉ ኢትዮጵያዊያን ስደተኛ ሰራተኞችን ደህንነት ማስጠበቅ ያደረገ ስምምነት ለመፈራረም ቅድመ ዝግጅቱ ተጠናቋልም ብለዋል።
በቀጣይም ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ከሚጓዙባቸው ሀገራት እንደ ጅቡቲ፣ ኬንያ፣ ባህሬን እና ሌሎች የአረብ ሀገራት ጋር ተመሳሳይ ስምምነቶች እንደሚደረጉም ተገልጻል።
በዓለም አቀፉ የሰራተኞች ድርጅት (አይኤልኦ) የአፍሪካ ቀንድ አስተባባሪ አሌክሲዮ ሙሲንዶ በበኩላቸው የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ አሰሪዎች ፌዴሬሽን ስምምነት በስደተኛ ሰራተኞች ላይ የሚደርስን መገለል፣ ጥቃት እና የሰራተኛን ደህንነት የሚያስጠብቅ ነው ብለዋል።
የአፍሪክ ቀንድ ሀገራት በርካታ ዜጎች ወደ እርስ በርስ ሀገራት እና ወደ መካከለኛው ምስራቅ ሀገራት በሚጓዙበት ወቅት የተለያዩ እንግልቶችን እያስተናገዱ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
አይኤልኦ ከኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በተጨማሪም ተመሳሳይ የሰራተኞች ደህንነት ሌሎች ሀገራትም በጋራ እንዲሰሩ እና ስምምነቶችን እንዲያደርጉ ድጋፍ እንዲሁም ግፊት በማድረግ ላይ እንደሆነም ገልጿል።
አይኤልኦ ከአንድ ኣመት በፊት ከጥር እስከ ጥቅምት ባሉት ወራት ውስጥ በምስራቅ በኩል ብቻ ከ200 ሺህ በላይ ዜጎች ወደ መካከለኛው ምስራቅ መጓዛቸውን አስታውቋል።
በኢትዮጵያ ከ250 ሺህ በላይ ሶማሊያዊያን ስደተኞች እንዲሁም ከ35 ሺህ በላይ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በሶማሊያ እንዳሉ የተመድ ሪፖርት ያስረዳል።