እስራኤል በሄዝቦላ የሮኬት ጥቃት 12 ሰዎች መገደላቸውን ገለጸች
የእስራኤል ባለስልጣናት በኢራን በሚደገፈው ሄዝቦላ ላይ የአጸፋ ምላሽ እንደሚሰጡ ዝተዋል
ሄዝቦላ ባለፈው ጥቅምት ወር የጋዛ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ በእስራኤል ቁጥጥር ስር ባለ ግዛት ለደረሰው ከባድ ጥቃት እጁ እንደሌለበት አስተባብሏል
እስራኤል በሄዝቦላ የሮኬት ጥቃት 12 ሰዎች መገደላቸውን ገለጸች።
በእስራኤል ቁጥጥር ስር በሚገኘው የጎላን ሀይት ውስጥ በሚገኝ የእግርኳስ ሜዳ ላይ በተፈጸመ ጥቃት ህጻናትን ጨምሮ 12 ሰዎች መገደላቸውን የገለጹት የእስራኤል ባለስልጣናት ለጥቃቱ ሄዝቦላን ተጠያቂ አድርገዋል።
ባለስልጣናቱ በኢራን በሚደገፈው ሄዝቦላ ላይ የአጸፋ ምላሽ እንደሚሰጡ ዝተዋል።
ሄዝቦላ ባለፈው ጥቅምት ወር የጋዛ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ በእስራኤል ቁጥጥር ስር ባለ ግዛት ለደረሰው ከባድ ጥቃት እጁ እንደሌለበት አስተባብሏል።
ጥቃቱ ከጋዛው ግጭት በትይዩ ያለውን ግጭት ያባባሰው ሲሆን በሁለቱ ተቀናቃኞች መካከል አጠቃላይ ጦርነት ሊቀሰቀስ ይችላል የሚለው ስጋት እንዲጨምር አድድጓል። የሮኬት ጥቃቱ የደረሰው እስራኤል በፈረንጆቹ 1967 ያካሄደችውን የመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት ተከትሎ በያዘችው ጎላን ኃይት ውስጥ ዱሬዝ መንደር በሚገኝ የእግርኳስ ሜዳ ላይ ነው።
"ሄዝቦላ ከባድ ዋጋ ይከፍላል" ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ከዱሬዝ ማህበረሰብ መሪ ጋር ባደረጉት የስልክ ውይይት መናገራቸውን ጽ/ቤታቸው ገልጿል።
ሄዝቦላ ባሰራጨው የጹህፍ መግለጫ "እስላማዊ ቡድኑ ከክስተቱ ጋር በፍጹም የሚያገናኘው ነገር የለም፤ የሚቀርቡትን የሀሰት ክሶች አይቀበልም" ብሏል።
ሄዝባላ ቀደም ሲል የእስራኤል ወታደራዊ ይዞታዎችን ኢላማ ያደረጉ በርካታ የሮኬት ጥቃት ማድረሱን አስታውቆ ነበር። የእስራኤል አምቡባንስ አገልግሎት በህጻናት እና ታዳጊዎች ተሞልቶ በነበረው ሜዳ ላይ በደረሰው የሮኬት ጥቃት ተጨማሪ 13 ሰዎች መቁሰላቸውን ገልጿል።
በእስራኤል እና ሊባኖስ ድንበር ያለው ግጭት እንዳይባባስ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት እያደረገች ያለችው አሜሪካ ጥቃቱን ዘግናኝ ስትል ያወገዘችው ሲሆን እስራኤል በኢራን ከሚደገፈው ሄዝቦላ ጋር በምታደርገው ውጊያ ያልተቋረጠ ድጋፍ እንደምታደርግም ገልጻለች።
እስራኤልን፣ ኢራንን፣ የፍልስጤም አስተዳደር እና ሀማስን ጨምሮ በመካከለኛው ምስራቅ ቁልፍ ሚና ካላቸው ሀገራት ጋር ግንኘነት ያላት ሞስኮም ጥቃቱን አውግዛለች።
"በሽብርኞች የሚካሄድን ማንኛውንም ጥቃት እናወግዛለን" ሲል የሩሲያው ታስ የዜና አገልግሎት የሩሲያን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭን ጠቅሶ ዘግቧል።
የእስራኤል ጦር ሮኬቱ የተተኮሰው በደቡብ ሊባኖስ ቸዳ ከሚባለው መንደር ሰሜን በኩል ከሚገኝ ቦታ ነው ብሏል።
የእስራኤል ጦር ቃል አቀባይ ሪር አድሚራል ዳንኤል ሀጋሪ ሮኬቱ ኢራን ሰራሽ ፋራቅ-1 በምርመራ ተደርሶበታል ብለዋል።