ሄዝቦላህ ወደ እስራኤል ከ200 በላይ ሮኬቶችን ተኮሰ
የሊባኖሱ ቡድን ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዡ ከተገደሉበት በኋላ በእስራኤል የጦር ጣቢያዎች ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶችን መፈጸሙን አስታውቋል
የእስራኤል ጦር በበኩሉ አብዛኞቹ ሮኬቶች ተመተው መውደቃቸውን ከመግለጽ ውጭ ጉዳት ስለመድረሱ ያለው ነገር የለም
ሄዝቦላህ በዛሬው እለት ወደ እስራኤል ከ200 በላይ ሮኬቶችን ተኮሰ።
የሊባኖሱ ቡድን ከፍተኛ አዛዡ በእስራኤል የአየር ጥቃት መገደሉን ተከትሎ ነው በርካታ ሮኬቶችን የተኮሰው።
የእስራኤል ጦር ሄዝቦላህ ወደ ጎላን ኮረብቶች እና ሌሎች የደቡባዊ እስራኤል ክፍሎች ከ200 በላይ ሮኬቶችን መተኮሱንና 20 ድሮኖች የእስራኤልን የአየር ክልል ጥሰው መግባታቸውን አስታውቋል።
ጦሩ አብዛኞቹ ሮኬቶች ተመተው መውደቃቸውን የገለጸ ሲሆን፥ እስካሁን ስለደረሰው ጉዳት ያለው ነገር የለም።
የሄዝቦላህን ጥቃት ተከትሎ እስራኤል በደቡባዊ ሊባኖስ ራምየህ እና ሃውላ በተባሉ አካባቢዎች ቡድኑ የሚገለገልባቸውን ህንጻዎች ማፈራረሷን ገልጻለች።
የሊባኖስ ብሄራዊ የዜና ወኩል ናሽናል ኒውስ የእስራኤል የጦር ጄቶች በሀገሪቱ የተለያዩ ከተሞች ድብደባ መፈጸማቸውንና በሃውላ በተፈጸመ የድሮን ጥቃት የአንድ ሊባኖሳዊ ህይወት ማለፉን ዘግቧል።
እስራኤል በትናንትናው እለት ሄዝቦላህ በደቡባዊ ሊባኖስ ካሉት ሶስት ክፍለጦሮች አንደኛውን የሚመራውን ሞሀመድ ናሜህ ናስር መግደሏን ይፋ አድርጋለች።
ሄዝቦላህ ለመጨረሻ ጊዜ ከእስራኤል ጋር ጦርነት በገጠመበት ወቅት (2006) የተሳተፈው ናስር፥ ለቡድኑ ወሳኝ ከሚባሉ አዛዦች መካከል አንዱ ነበር።
እስራኤል ለወራት በሊባኖስ በፈጸመቻቸው የአየር ጥቃቶች ሌሎች ሁለት የሄዝቦላህ አዛዦችን መግደሏ ይታወሳል።
የትናንቱን የናስር ግድያ ተከትሎም በኢራን ድጋፍ እንደሚደረግለት የሚነገርለት ሄዝቦላህ በእስራኤል ላይ የአጻፋ እርምጃውን ማጠናከሩን አሶሼትድ ፕረስ ዘግቧል።
አሜሪካ እና ፈረንሳይ የሊባኖስ እና እስራኤል የድንበር ውጥረትን ለማርገብ ጥረት እያደረጉ ነው ቢባልም እስካሁን ጦርነቱን የሚያስቀር መፍትሄ አልተገኘም።
ሄዝቦላህ የኔታንያሁ አስተዳደር በጋዛ የሚፈጽመውን ድብደባ ካላቆመ የሮኬት ጥቃቱ እንደሚቀጥል ማሳሰቡን ገፍቶበታል።
እስራኤልም ሄዝቦላህ ጥቃቱን ከገፋበት እግረኛ ጦሬን አስገብቼ “ሊባኖስን ወደ ድንጋይ ዘመን” እመልሳታለሁ ስትል መዛቷ አይዘነጋም።
ከ150 ሺህ በላይ ሮኬቶች እና ሚሳኤሎችን መታጠቁ የሚነገርለት ሄዝቦላህ ለእስራኤል ደህንነት ትልቅ ስጋት ፈጥሯል።