እስራኤል ከሄዝቦላ ጋር ጦርነት ውስጥ ብትገባ አሜሪካ ድጋፍ እንደምታደርግ አስታወቀች
የእስራኤል ከፍተኛ ልኡክ ከአሜሪካ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪዎች ጋር በዋሽንግተን ውይይት አድርጓል
ወደ ሊባኖስ እና ቴልአቪቭ ልኡክ ልኮ ለማሸማገል ጥረት ሲያደርግ የነበረው የጆ ባይደን አስተዳደር ለጦርነቱ ድጋፍ አደርጋለሁ ማለቱ መነጋገርያ ሆኗል
በአስራኤል እና ሄዝቦላ መካከል ሁሉን አቀፍ ጦርነት ቢጀመር አሜሪካ ለእስራኤል ወታደራዊ ድጋፍ እንደምታደርግ አስታወቀች፡፡
በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለው ውዝግብ ወደ ለየለት ጦርነት እንዳያመራ ወደ ሊባኖስ እና ቴልአቪቭ ልኡክ ልኮ ለማሸማገል ጥረት ሲያደርግ የነበረው የጆ ባይደን አስተዳደር ለጦርነቱ ድጋፍ አደርጋለሁ ማለቱ መነጋገርያ ሆኗል፡፡
በሄዝቦላ እና በእስራኤል መካከል ድንበር አቋራጭ የሚሳይል ተኩስ ከሰሞኑ ተባብሶ መቀጠሉን ተከትሎ እስራኤል በሊባኖስ ሁሉን አቀፍ ወታደራዊ ዘመቻ ልታደርግ እንደምትችል ማስጠንቀቋ አይዘነጋም፡፡
ሄዝቦላ በበኩሉ በሊባኖስ ላይ ጦርነት ማወጅ እስራኤልን ከፍተኛ ዋጋ ያስከፍላል በሚል ምላሽ ሰጥቷል፡፡
በሳምንቱ መጨረሻ ወደ ዋሽንግተን ያቀኑት የእስራኤል የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ዛቺ ሄነግቢ እና የስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ሚኒስትሩ ሮን ደርመር ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን እና ከብሔራዊ ደህንነት አማካሪው ጃክ ሱሊቫኒ ጋር ተወያይተዋል፡፡
ልኡኩ በቆይታው በጋዛ የሚገኙ ታጋቾችን በሚመለከት፣ የተኩስ አቁም ስምምነት፣ በሰሜን የእስራኤል ድንበር ስለሚገኝው የጦርነት ስጋት እንዲሁም ኢራንን በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት አድርጓል፡፡
ሄዝቦላን በተመለከተ ባደረጉት ውይይት አሜሪካ ጦሯን ወደ ስፍራው በመላክ በጦርነቱ በቀጥታ ባትሳተፍም ሌሎች ወታደራዊ ድጋፎችን ግን ለቴልአቪቭ ለመስጠት ቃል ገብታለች፡፡
በሄዝቦላ እና በእስራኤል መካከል ያለው መካረር ወደ ለየለት ቀጠናዊ ግጭት እንዳያማራ ሁለቱ ወገኖች ሁኔታዎችን እንዲያለዝቡ ሲጠይቅ የነበረው የባይደን አስተዳደር ለእስራኤል የሰጠው ወታደራዊ ድጋፍ ማስተማመኛ የጦርነቱን አይቀሬነት አመላካች ነው ያሉ ተንታኞች፤ በመካከለኛው ምስራቅ ያለው የሰላም ሁኔታ ወደ ቀጠናዊ ብጥብጥ ሊያመራ እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡
በሀገር ቤት እና በአለም አቀፍ ደረጃ በከፍተኛ ጫና ውስጥ የሚገኝው የኔታንያሁ አስተዳደር የጋዛውን ጦርነት ባልቋጨበት ሁኔታ ወደ አዲስ ጦርነት መግባቱ አደገኛ ውሳኔ እንደሚሆንም ተንታኞች አክለው ገልጸዋል፡፡
ለዘጠኝ ወራት ከሃማስ ጋር የተራዘመ ጦርነት ውስጥ የሚገኝው የእስራኤል ጦር አሁን በሚገኝበት ሁኔታ ሌላ ጦርነት ለማስተናገድ በሙሉ ቁመና ላይ እንደማይገኝ ቀደም ብለው የወጡ ዘገባዎች አመላክተዋል፡፡
ሄዝቦላ እና እስራኤል ወደ ለየለት ጦርነት የሚመሩ ከሆነ ኢራንን ጨምሮ ሌሎች ቀጠናዊ ተዋናዮች ተሳታፊ መሆን ግጭቱን ሊያባበሰው እንደሚችል ሲኤንኤን በዘገባው አመላቷል፡፡
በየመን የሚገኙት ሀውቲዎች እንዲሁም በኢራቅ እና በሶርያ የሚገኙ የቴሄራን ከፍተኛ ድጋፍ ያላቸው ታጣቂዎች በጦርነቱ በግልጽ ሊሳተፉ እንደሚችሉ ይጠበቃል፡፡
ላለፉት ሁለት አስርተ አመታት ከሽብረኝነት ጋር በተያያዘ በተከፈተበት ጦርነት አሁንም በርካታ በቅጡ መረጋጋት የተሳነው ፖለቲካ የሚመሩ ሀገራት ያሉበት የመካከለኛው ምስራቅ ቀጠና የእስራኤል እና ሄዝቦላ ጦርነት ተጨማሪ ስጋት አንዣቦበታል፡፡