ዩኤኢ በ2021 ከኢንዱስትሪ ምርቶች ወጪ ንግድ 120 ቢሊዮን ድርሃም ማግኘቷን አስታወቀች
በዩኤኢ 2 ሺ 577 ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች ተሰማርተው ይገኛሉ
ዩኤኢ በ2030 ከኢንዱስትሪ ዘርፍ 300 ቢሊዮን ድርሃም ገቢ ለማግኘት አቅዳለች
የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች በተጠናቀቀው 2021 ወደ ውጭ አገራት ከተላኩ ኢንዱስትሪ ምርቶች 120 ቢሊዮን ድርሃም ገቢ አገኘች፡፡
ዩኤኢ ወደ ተለያዩ አገራት ከተላኩ የኢንዱስትሪ ምርቶች 120 ቢሊዮን ድርሃም ገቢ ማግኘቷን የኢንዱስትሪ እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ሱልጣን ቢን አል ጃቢር (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
የተገኘው ገቢ በአገሪቱ ታሪክ ከፍተኛው መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ ይህ ዘርፍ የበለጠ እንዲዘምን እና የተሻለ ገቢ እንዲያስገኝ የሚያስችሉ ስራዎች እንደሚከናወኑ ገልጸዋል፡፡
በዚሁ በተጠቀሰው ዓመት 220 አዳዲስ ዓለም አቀፍ ፋብሪካዎች በዩኤኢ ስራ የጀመሩ ሲሆን በተያዘው አዲስ ዓመት ተጨማሪ ኢንዱስትሪዎች እንዲቋቋሙና ምርታማነታቸውን መጨመር የሚያስችሉ ድጋፎች እንደሚደረጉ ሚኒስትሩ አክለዋል፡፡
ዩኤኢ ከኢንዱስትሪ ምርቶች የምታገኘውን ገቢ በ2030 ወደ 300 ቢሊዮን ድርሃም ከፍ ለማድረግ ማቀዷን ቀደም ሲልም አስታውቃለች፡፡
ወደፊት ይህን ጨምሮ የሀይድሮጂን እና የጠፈር ሳይንስን የሚደግፉ ግብዓቶችን ለማምረት የሚያስችሉ ኢንዱስትሪዎች እንደሚቋቋሙም ገልጻለች፡፡
እንደ ተመድ የኢንዱስትሪ እና የልማት ድርጅት የ2021 ዓመታዊ ሪፖርት ከሆነ ዩኤኢ በኢንዱስትሪዎች ልማት ከዓለም አቀፍ አገራት በ30ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡
በተጠናቀቀው የፈረንጆቹ ዓመትም 20 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መሳቧ ይታወሳል፡፡
በዚህም ከመካከለኛው ምስራቅ ዓረብ አገራት መካከል ቀዳሚ ከዓለማችን ደግሞ ዘጠነኛዋ የኢንቨስትመንት መዳረሻ አገር ሆናለች ተብሏል፡፡
ባለፉት 10 ዓመታት ውስጥ በዩኤኢ ገንዘባቸውን ያፈሰሱ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ቁጥር በ52 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡
በአጠቃላይ በዩኤኢ 2ሺህ 577 ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ የተሳተፉ ሲሆን የ114 አገራት ዜግነት ያላቸው ሰዎችም በአገሯ በስራ ላይ ናቸው፡፡