ጉብኝቱ በመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት አዲስ ትብብር ያመጣል ተብሎለታል
የቱርኩ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን ከሳምንታት በኋላ በተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች (ዩ.ኤ.ኢ) ጉብኝት እንደሚያደርጉ አስታወቁ።
ፕሬዝዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን በየካቲት ወር ላይ ወደ አቡዳቢ በማቅናት ከዩኤኢ አመራሮች ጋር እንደሚመክሩም ተገልጿል።
የፕሬዝዳንቱ ጉብኝት በአካባቢው ሀገራት መካከል አዲስ የትብብር መንገድ እንደሚከፍት ተገልጿል።
ፕሬዝዳንት ኤርዶሃን ከብሄራዊ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቃለመጠይቅ በፈረንጆቹ የካቲት 14 ቀን ወደ አቡዳቢ ለይፋዊ የስራ ጉብኝት እንደሚያቀኑ ተናግረዋል።
ባለፉት ዓመታት የተባበሩት አረብ ኢምሬት እና የቱርክ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በሚፈለገው ደረጃ ላይ ያልነበረ ሲሆን ከቅርብ ጊዜ አንስቶ ሁለቱ ገገራት ግንኙነታቸውን ለማሻሻል በመጣር ላይ መናቸውን የቱርክ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካቩሶግሉ ከዚህ በፊት በሰጡት መግለጫ ላይ መናገራቸው ይታወሳል።
የዩኤኢ ምክትል ጦር አዛዥ እና የአቡዳቢ ልዑል አልጋ ወራሽ ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ አልናህያን ባሳለፍነው ህዳር ወር ላይ አንካራን መጎብኘታቸው ይታወሳል።
ቢን ዛይድ በቱርክ በነበራቸው ቆይታ ከፕሬዝዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን እና ሌሎች የቱርክ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር በሁለትዮሽ እና አካባቢያው ጉዳዮች ዙሪያ መወያየታቸውም አይዘነጋም።