እስራኤል በጋዛ በዋናነት ሆስፒታሎች ላይ አነጣጥራ በፈጸመችው ጥቃት 120 ሰዎች ተገደሉ
ይህ የሟቾች ቁጥር የተመዘገበው ባለፉት 48 ሰአታት በተፈጸሙ የአየር ጥቃቶች ነው
ሀማስ ህዝባዊ ተቋማትን ለመሸሸጊያነት እንደሚጠቀም እስራኤል በተደጋጋሚ ትከሳለች
እስራኤል በጋዛ ሰርጥ ባለፉት 48 ሰአታት በፈጸመችው የአየር ጥቃት 120 ፍልስጤማውያን መገደላቸው ተነገረ፡፡
በሰሜናዊው ጋዛ በሚገኝ ሆስፒታል በደረሰው ጥቃት ከሞቱት ሰዎች ባለፈ የህክምና ሰራተኞች መቁሰላቸው እና የህክምና መሳሪያዎች ላይ ጉዳት መድረሱን የፍልስጤም የህክምና ባለስልጣናት ገልጸዋል፡፡
ከሟቾቹ መካከል በጋዛ ከተማ ዜይቱን በተባለ አካባቢ የሚኖሩ ሰባት የአንድ ቤትሰብ አባላት የሚገኙበት ሲሆን የተቀሩት በማዕከላዊ እና ደቡባዊ ጋዛ በተፈጸመ ጥቃት የሞቱ ናቸው፡፡
የእስራኤል ወታደሮች ካለፈው ወር መጀመሪያ ጀምሮ በሰሜናዊዉ ጋዛ የምድር እና የአየር ጥቃታቸውን አጠናክረዋል።
“የቀጠለው ጥቃት አካባቢውን ሙሉ ለሙሉ በዘላቂነት ከነዋሪዎች ለማጽዳት ያለመ መሆኑን” ፍልስጤማውያን ሲናገሩ፤ እስራኤል በበኩሏ የሰሜናዊ ጋዛ ዘመቻ የሃማስ ተዋጊዎች በአካባቢው ጥቃት እንዳይፈጽሙ እና እንደገና እንዳይሰበሰቡ ለማድረግ ያለመ መሆኑን ትገልጻለች፡፡
በጋዛ ሰሜናዊ ጫፍ ላይ ከሚገኙት ሶስት የህክምና ተቋማት መካከል አንዱ የሆነው ካማል አድዋን ሆስፒታል ዳይሬክተር ሁሳም አቡ ሳፊያ “እየተካሄደ ያለው የእስራኤል የቦምብ ጥቃት ወረራው ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ተቋሙን አንለቅም ያሉትን የሆስፒታሉ ሰራተኞችን ለቀው እንዲወጡ ለማስገደድ ያለመ ይመስላል” ብለዋል፡፡
ትናንት (አርብ) ከቀትር በኋላ እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ የቦምብ ጥቃቱ በቀጥታ ወደ የድንገተኛ ህመምተኞች መቀበያ መግቢያ በር ላይ በተደጋጋሚ ያነጣጠረ ነበር ያሉት ዳይሬክተሩ በጥቃቱ ዶክተሮች እና ነርሶችን ጨምሮ 12 ሰራተኞች መቁሰላቸውን ተናግረዋል፡፡
በሰዎች ላይ ከደረሰው ጉዳት ባለፈም የሆስፒታሉ የኤሌክትሪክ ጄነሬተር፣ የኦክስጂን አውታር እና የውሃ አቅርቦት መስተጓጎሉ ነው የተሰማው።
ጥቃቱን አስመልክቶ የተጠየቀው የእስራኤል ጦር በበኩሉ በሆስፒታሉ ላይ ጥቃት ስለመፈጸሙ እንደማያውቅ ገልጿል፡፡
ሃማስ ሆስፒታሎችን እና ንጹሀንን ለመደበቂያነት እንደሚጠቀም የሚናገረው የእስራኤል ጦር ይህን ክሱን የሚደግፉ የተለያዩ ቪዲዮዎችን እና ፎቶዎችን አሰራጭቷል፡፡
ውንጀላውን ውድቅ የሚያደርገው ሃማስ ደግሞ ንጹሀንን እና ህዝባዊ ተቋማትን ለወታደራዊ አገልግሎት እንደማይጠቀም ተናግሯል።
እስራኤል በጋዛ ለ13 ወራት ባስቀጠለችው ጦርነት ከ44 ሺ በላይ ሰዎች ሲገደሉ ቢያንስ አንድ ጊዜ ሁሉም የጋዛ ነዋሪዎች ከቀያቸው መፈናቀላቸውን የጋዛ ባለስልጣናት ገልጸዋል።