እስራኤል ማዕከላዊ ቤይሩትን ያናወጠ ጥቃት ፈጸመች
በቤይሩት ከተማ ባስታ ሰፈር በተፈጸመው ጥቃት ቢያንስ አራት ሰዎች መገደላቸው እና ሌሎች 23 ደግሞ መቁሰላቸው ተገልጿል
እስራኤል ይህን ጥቃት የፈጸመችው አሜሪካ ሰራሹን 'በንከር በስተር' ቦምብ ተጠቅማ ነው ተብሏል
እስራኤል ማዕከላዊ ቤይሩትን ያናወጠ ጥቃት መፈጸሟ ተገለጸ።
በኢራን በሚደገፈው ሄዝቦላ ላይ እየፈጸመች ያለውን ጥቃት አጠናክራ የቀጠለችው እስራኤል በትናንትናው እለት ማዕከላዊ ቤይሩትን ያናወጠ ጥቃት መፈጸሟን ሮይተርስ የጸጥታ ምንጮችን ጠቅሶ ዘግቧል።
በቤይሩት ከተማ ባስታ ሰፈር በተፈጸመው ጥቃት ቢያንስ አራት ሰዎች መገደላቸውን እና ሌሎች 23 ደግሞ መቁሰላቸውን የሄዝቦላ አል ማናር ቴሌቪዥን ጤና ሚኒስቴርን ጠቅሶ ዘግቧል።
የሊባኖስ ዜና አገልግሎት በጥቃቱ በሰዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን እና ባለስምንት ወለል ህንጻ መውደሙን ዛሬ ማለዳ ዘግቧል። በሊባኖሱ አል ጀዲድ ቴሌቪዥን ጣቢያ የተላለፈው ቪዲዮ አንድ ሙሉ በሙሉ የወደመ ህንዳ እና በዙሪያው የተጎዱ ሌሎች ህንጻዎችን አሳይቷል።
እንደ ቴሌቪዥን ጣቢያው ዘገባ ከሆነ እስራኤል ይህን ጥቃት የፈጸመችው 'በንከር በስተር' ቦምብ ተጠቅማ ነው። ሮይተርስ የአይን እማኞችን ጠቅሶ እንደዘገበው ከሆነ ቅዳሜ ጠዋት የተፈጸመው ጥቃት ከተማዋን አናውጧል።
የጸጥታ ምንጮች እንደሚሉት ከሆነ ቢያንስ አራት ቦምቦች ተጥለዋል።
እስራኤል በሄዝቦላ በተያዘው የከተማው ደቡባዊ ዳርቻ ላይ የአየር ጥቃት ስትፈጽም በዚህ ሳምንታት ውስጥ ለአራተኛ ጊዜ ነው። እስራኤል ባለፈው በማዕከላዊ ቤይሩት ራስ አል ናባ ግዛት በፈጸመችው ጥቃት የሄዝቦላ ሚዲያ ኃላፊን መግደሏ ይታወሳል።
እስራኤል የረጅም ጊዜ ጠላቷ እና በቀጣናው የኢራን ዋነኛ አጋር የሆነውን ሄዝቦላ በርካታ መሪዎችን በደቡባዊ ቤይሩት በፈጸመችው የአየር ጥቃት ገድላለች።
እስራኤል ከጋዛው ጦርነት ጎን ለጎን ለአንድ አመት ያህል ከሄዝቦላ ጋር ድንበር አካባቢ የተኩስ ልውውጥ ካደረገች በኋላ ባለፈው መስከረም ወር ከባድ የአየር የአየር እና የእግረኛ ጦር ጥቃት ከፍታለች።
እስራኤል እና ሄዝቦሃ ወደ ግጭት የገቡት፣ ሄዝቦላ በጋዛ ከእስራኤል ጋር እየተዋጋ ላለው ሀማስ አጋርነት ለማሳየት ተኩስ በመጀመሩ ምክንያት ነበር።