"እስራኤል በጋዛ ጦርነት በቀጠለችበት ወቅት ሃማስ ታጋቾችን ከለቀቀ እብደት ነው" - ካሊል አል ሃያ
የኔታንያሁ አስተዳዳር በበኩሉ የፍልስጤሙ ቡድን በድጋሚ እንዳይደራጅ በሚል በሰሜናዊ ጋዛ ጥቃቱን አጠናክሯል
አሜሪካ በጋዛ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተኩስ እንዲቆም በጸጥታው ምክርቤት የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ ውድቅ አድርጋለች
ሃማስ እስራኤል በጋዛ የምታካሂደውን ጦርነት ካላቆመች የታጋቾች እና እስረኞች ልውውጥ ስምምነት ላይ እንደማይደርስ ገለጸ።
በጋዛ ሰርጥ የሃማስ ጊዜያዊ መሪ ካሊል አል ሃያ ከአል አቅሳ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቆይታ "ወረራው ካልቆመ የነጻነት ታጋይ ቡድን በተለይም ሃማስ እንዴት ታጋቾችን ይለቃል? (እስራኤል) ጦርነቱን በቀጠለችበት ሁኔታ ሃማስ ዋነኛ ካርዱን ከጣለ እብደት ነው" ሲሉ ተደምጠዋል።
የመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክርቤት በትናንትናው እለት በጋዛ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተኩስ እንዲቆም የቀረበው የውሳኔ ሃሳብ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት ባላት አሜሪካ ውድቅ ተደርጓል።
በተመድ የአሜሪካ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድ በዚሁ ወቅት ሀገራቸው የውሳኔ ሃሳቡን የምትደግፈው የእስራኤል ታጋቾች በፍጥነት የሚለቀቁበት የተኩስ አቁም ስምምነት ከተፈረመ ብቻ ነው ብለዋል።
በጸጥታው ምክርቤት የቀረቡ የጋዛ የተኩስ አቁም የውሳኔ ሃሳቦችን ውድቅ ያደረገችው ዋሽንግተን የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጦርነቱን ለማስቀጠል የያዙትን እቅድ እየደገፈች ነው ሲል ሃማስ ይከሳል።
ከኳታርና ግብጽ አደራዳሪ ቡድኖች ጋር በተደረጉ ምክክሮች ሃማስን ወክለው የተገኙት ካሊል አል ሃያ ቡድኑ አሁንም ከተለያዩ ሀገራት የሚቀርቡ የእናደራድር ጥያቄ በአዎንታ እንደሚመለከተው ጠቅሰው ኔታንያሁ ድርድሩን እያጓተቱ ነው ብለዋል።
ከትናንት በስቲያ በጋዛ ጉብኝት ያደርጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንታሁ ከጦርነቱ መጠናቀቅ በኋላ ሃማስ ጋዛን እንደማይመራ መናገራቸው ይታወሳል።
በጋዛ 101 ታጋቾች በህይወት እንዳሉ እንደሚታመን በመጥቀስም እነዚህን ታጋቾች ወደ እስራኤል ለሚያስመልሱ በነፍስ ወከፍ 5 ሚሊየን ዶላር ሽልማት እንደሚሰጣቸው መግለጻቸውን ሬውተርስ ዘግቧል።
እስራኤል በትናንትናው እለት በሰሜናዊ ጋዛ ቤት ላሂያ በሚገኝ ሆስፒታል ላይ በፈጸመችው ጥቃት በርካታ ሰዎች ህይወታቸው ማለፉን የጋዛ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል። አሁንም ድረስ በፍርስራሽ ውስጥ የሚገኙትን የማውጣት ርብርቡ መቀጠሉን ቢቢሲ ዘግቧል።
የመንግስታቱ ድርጅት እስራኤል በሰሜናዊ ጋዛ ዳግም የተጠናከረ ጥቃት ከከፈተች ጀምሮ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን ከበባ ውስጥ ናቸው፤ ለ40 ቀናት ምንም ሰብአዊ ድጋፍ አላገኙም ብሏል።
44 ሺህ የሚጠጉ ፍልስጤማውያንን የተገደሉበት የእስራኤልና ሃማስ ጦርነት 103 ሺህ 898 ሰዎችን አቁስሎም በተኩስ አቁም ስምምነት ሊቆም አልቻለም።