በባርሴሎና እና ማድሪድ ጨዋታ ወቅት የዘረኝነት ስድብ ያሰሙ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ
ጨዋታውን ባርሴሎና ተቀናቃኙን ሪያል ማድሪድን 4-0 በሆነ ውጤት ሲያሸንፍ ያማል ግብ ካስቆጠሩት መካከል ይገኝበታል።
የስፔን እግርኳስ ፌደሬሽን(አርኤፍኢኤፍ) ባወጣው መግለጫ የዘረኝነት ጥቃቱን "ማህበራዊ እርግማን" ሲል ገልጾታል
በባርሴሎና እና ማድሪድ ጨዋታ ወቅት የዘረኝነት ስድብ ያሰሙ ግለሰቦች በቁጥጥር ዋሉ።
ባርሴሎና እና ሪያልማድሪድ ባለፈው ጥቅምት ወር በተጋጠሙበት ወቅት በሁለት የባርሴሎና ተጨዋቾች ላይ የዘረኝነት ስድብ ሰንዝረዋል የተባሉ ሶስት ሰዎች መያዛቸውን የስፔን ፖሊስ በዛሬው እለት አስታውቋል።
የኢኳቶሪያል ጊኒ እና የሞሮኮ ዝርያ ያለው የባርሴሎናው አጥቂ ላሚን ያማል በበርናባው ስቴዲየም በተደረገው ጨዋታ ወቅት የጥላቻ እና የዘረኝነት ስድብ ከተሰነዘረባቸው ተጨዋቾች መካከል አንዱ ነው።
ጨዋታውን ባርሴሎና ተቀናቃኙን ሪያል ማድሪድን 4-0 በሆነ ውጤት ሲያሸንፍ ያማል ግብ ካስቆጠሩት መካከል ይገኝበታል።
የስፔን ብሔራዊ ፖሊስ በኤክስ ገጹ "ባለፈው ጥቅምት ወር በተካሄደው የኤልክላሲኮ ጨዋታ በሁለት ተጨዋቾች ላይ የዘረኝነት ስድብ የተሳደቡ ሶስት ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል"ብሏል።
"የተያዙት ግለሰቦች የሁለቱን የእግርኳስ ተጨዋቿች የሞራልና ስብእና የሚጎዳ የጥላቻ ንግግር አሰምተዋል።"የስፔን ሱፕሪም ስፓርትስ ካውንስል እና ላሊጋው ክስተቱን አውግዞታል።
"ላሊጋ በተጨዋቾቹ ላይ ሚደርስን የዘረኝነት ስድብ እና ምልክት የጥላቻ ወንጀልን ለሚመለከተው የብሔራዊ ፖሊስ መረጃ ብርጌድ ወዲያውኑ ያመለክታል" ብሏል ላሊጋ ባወጣው መግለጫ።
ሪያል ማድሪድ የግለሰቦቹን ማንነት ለማወቅ ምርመራ ከፍቷል።
የስፔን ማይግሬሽን ሚኒስትር ኢልማ ሴይዝ ክስተቱን አውግዘውታል።"እንዲህ አይነት ድርጊቶች እንዲለመዱ አንፈቅድም።"
የስፔን እግርኳስ ፌደሬሽን(አርኤፍኢኤፍ) ባወጣው መግለጫ የዘረኝነት ጥቃቱን እንደማይታገስ ገልጿል፤ ድርጊቱንም "ማህበራዊ እርግማን" ሲል ገልጾታል።
ባለፈው ጥቅምት ወር የስፔን ፖሊስ በብራዚላዊው የሪያል ማድረድ አጥቂ ቪንኪየስ ጁኒየር ላይ በማህበራዊ ሚዲያ የጥላቻ ንግግር ዘመቻ ከፍተዋል ያላቸውን አራት ሰዎች መያዙን ገልጾ ነበር።