የኢትዮጵያን የዲሞክራሲ ሽግግር እንደሚደግፉ 13 ሀገራት በጋራ ባወጡት መግለጫ አስታወቁ
የአውሮፓ ህብረትን ጨምሮ 13 ሀገራት በምርጫው ዙሪያ ትዝብታቸውን ተናግረዋል
በኢትዮጵያ ግጭቶችን እና አለመግብባቶችን ለማስወገድ አሳታፊ ብሔራዊ ውይይት እንዲካሄድም ሀገራቱ ጠይቀዋል
የኢትዮጵያን የዲሞክራሲ ሽግግር እንደሚደግፉ 13 ሀገራት በአዲስ አበባው የዩናይትድ ኪንግደም ኢምባሲ በኩል ባወጡት የጋራ መግለጫ አስታወቁ።
በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት ቢሮን ጨምሮ ዋና መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ የካናዳ፤ ጀርመን፤ጃፓን ኖርዌይ፤አውስትራሊያ፤ ዴንማርክ፤ ኔዘርላንድ ፤ኒውዝላንድ እና አየርላንድ በእንግሊዝ ኢምባሲ በኩል ምርጫውን አስመልክቶ መግለጫ አውጥተዋል።
እነዚህ አገራት በእንግሊዝ በኩል ባወጡት መግለጫ እንዳሉት ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከምርጫው ጋር በተያያዘ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ፤የሲቪል ማህበረሰብ እና ሚዲያዎች ላይ መልካም ስራ አስመዝግቧል ብለዋል።
የሲቪል ማህበረሰብ ተቋማት ዜጎችን ስለምርጫው በማስተማር እና የምርጫውን ሂደት ከመደገፍ ጀምሮ በመታዘብ ጥሩ ስራ መስራታቸውንም አገራቱ አክለዋል።
የምርጫው ዕለት በርካቶች መራጮችን ለመርዳት አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ተቋቁመው በሌሊት ሳይቀር መስራታቸውን እንደታዘቡም እነዚህ አገራት መታዘባቸውን ገልጸዋል።
ምርጫው የተገደበ እና ፈታኝ ፖለቲካዊ ሁኔታ ባለበት መካሄዱን የሚገልጸው ይህ መግለጫ የፖለቲካ እስረኞች፤የሚዲያ ተወካዮች እና የፓርቲዎች ጥቃት መፈጸሙንም አስታውቋል።
እንዲሁም የዘንድሮው መርጫው የተካሄደው የደህንነት ስጋት፤ ተፈናቃዮች መምረጥ እና መመረጥ በማይችሉበት ሁኔታ እና የሴቶች ተሳትፎ በቀነሰበት ሁኔታ እንደተካሄደ አገራቱ ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
ምርጫ ብቻውን ወደ ዲሞክራሲ አይወስድም ያሉት እነዚህ አገራት በኢትይጵያ የሚታዩ ግጭቶችን እና አለመግባባቶችን ለመፍትት ቀጣይ ሁሉን አካታች እና አሳታፊ ውይይት እንዲደረግ አሳስበዋል።