ልዩልዩ
በናይጄሪያ የሰርግ ፕሮግራም ታድመው ሲመለሱ የነበሩ ሰዎችን የጫነች ጀልባ ተገልብጣ የ13 ሰዎች ህይወት አለፈ
ሟቾቹ የአንድ ቤተሰብ ሰዎች ናቸው ተብሏል
በሀገሪቱ ባሳለፍነው ሳምንት በተመሳሳይ የጀልባ አደጋ ከ150 በላይ ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል
አደጋው የደረሰው በናይጄሪያ ሶኮቶ ግዛት ሻጊሪ በተሰኘ ወረዳ ውስጥ ነው፡፡
የአንድ መንደር ነዋሪዎች የሆኑ 18 ቤተሰቦች ፣ የሰርግ ዝግጅት ላይ ውለው በጀልባ ከዶሮዋ ወደ ጊንጋ መንደር በመጓዝ ላይ ነበሩ፡፡
ይሁንና ነዋሪዎቹ የሰርግ ፕሮግራሙን አጠናቀው በሚጓዙባት አነስተኛ ጀልባ ወደ ቤታቸው በመመለስ ላይ ሳሉ ፣ ጀልባዋ ተገልብጣ 13ቱ ህይወታቸው ሲያልፍ 5ቱ ብቻ በህይወት ሊተርፉ ችለዋል።
እነዚህ ሟች ዜጎች በአንድ አካባቢ ተሰባስበው የሚኖሩ የቤተሰብ አባላት እንደሆኑም የሲጂቲኤን ዘገባ ያመለክታል።
ለነዚህ ዜጎች ሞት ምክንያት የሆነችው ይህች አነስተኛ ጀልባ ረጅም ጊዜ ያገለገለች እንደሆነች የአካባቢው አስተዳድር ለመገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል።
በናይጀሪያ በጀልባ አደጋ ምክንያት የዜጎች ህይወት ሲያልፍ በተደጋጋሚ የተስተዋለ ሲሆን ባሳለፍነው ሳምንት 180 ሰዎችን ያሳፈረች ጀልባ ሰጥማ ከ 150 በላይ ሰዎች ህይወታቸው ማለፉ ይታወሳል።
የጀልባዎቹ ከአቅም በላይ መጫን ፣ የአየር ሁኔታው እና ያለጥገና ለረዥም ጊዜ ማገልገል በናይጄሪያ በተደጋጋሚ ለሚከሰቱ የጀልባ አደጋዎች በምክንያትነት ይጠቀሳሉ፡፡