ልዩልዩ
በናይጄሪያ በደረሰ የጀልባ መገልበጥ አደጋ ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር 81 ደረሰ
በነፍስ አድን ስራ እስካሁን የ22 ሰዎችን ህይወት ማትረፍ መቻሉ ተነግሯል
ጀልባዋ ኬቢ ከተባለች ገጠራማ ከተማ 170 ሰዎችን አሳፍራ ስትጓዝ ነበር
በናይጄሪያ በሳለፍነው ሳምንት በደረሰ የጀልባ መገልበጥ አደጋ ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር 81 መድረሱን የሀገሪቱ ባለስልጣናት አስታወቁ።
የጀልባ መገልበጥ አደጋው በሳለፍነው ረቡዕ በሰሜናዊ ናይጄሪያ በሚገኘው የኒጀር ወንዝ ላይ የደረሰ መሆኑም ተነግሯል።
ጀልባዋ ኬቢ ከተባለች ገጠራማ ከተማ የተነሳች ሲሆን፣ ጎረቤት ሀገር ኒጀር ወደሚገኝ የገበያ ስፍራ 170 ሰዎችን አሳፍራ ስትጓዝ እንደነበር ተገልጿል።
ከአቅም በላይ ሰዎችን ጭና የነበረችው ጀልባ ተገልብጣ በርካታ ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን የሲ.ጂ.ቲ.ኤን ዘገባ ያመለክታል።
የነፍስ አድን ሰራተኞች በወንዙ ላይ ባደረጉት አሰሳም እስካሁን የ81 ሰዎችን አስከሬን ማግኘታቸውን ነው የአካባው አስተዳዳሪ የተናገሩት።
በነፍስ አድን ስራው እስካሁን 22 ሰዎችን ህይወት ማትረፍ እንደተቻለ አስተዳዳሪው አቲኩ ባጉዱ ያስታወቁ ሲሆን፣ የነፍስ አድን ስራው መቀጠሉንም አስታውቀዋል።
በኒጀር ወንዝ ላይ የጀልባ አደጋዎች በተደጋጋሚ የሚያጋጥሙ ሲሆን፤ የአየር ጸባይ፣ አከቅም በላይ መጫን እና የጀልባዎች የቴክኒክ ችግሮች የአደጋው መንስኤዎች ናቸው ተብሏል።