በሱዳን ምዕራብ ዳርፉር በተነሳ የጎሳ ግጭት የሟቾች ቁጥር 132 ደረሰ
አሁን ላይ አካባቢው የተረጋጋ ሲሆን፣ በሚሊሻዎች መካካል ሲደረግ የነበረው የተኩስ ልውውጥ ጋብ ብሏል
በግጭቱ ከተሳተፉ ሚሊሻዎች ውስጥ የተወሰኑት ዳርፉርን ከሚያዋስኑ ጎረቤት ሀገራት የገቡ መሆናቸው ተገልጿል
በሱዳን የምዕራብ ዳርፉር ግዛት ዋና ከተማ አል-ጂኔይና በተከሰተ የጎሳ ግጭት 132 ሰዎች መሞታቸውን የምዕራብ ዳርፉር አስተዳዳሪ መሃመድ አብደላህ አልዶማህ አስታውቀዋል።
በግጭቱ ህይወታቸው ካለፈ ሰዎች በተጨማሪም 208 ሰዎች ላይ ጉዳት ደርሷል ብለዋል አስተዳዳሪው።
ግጭቱ የተከሰተው በአካባቢው በሚኖሩ የአረብ ጎሳ እና አረብ ባልሆኑ ማህበረሰቦች መካከል መሆኑ የተገለጸ ሲሆን በከተማዋ የሚኖሩ ከ700 ሺህ በላይ ነዋሪዎች በግጭቱ እንቅስቃሴያቸው ታውኮ ቆይቷል።
የዐይን እማኞች ለአል ዐይን ዜና እንደገለጹት፣ በአከባቢው ቤቶችን ማቃጠልን ጨምሮ በሁለት ጎሳዎች መካከል በሚደረጉ የተኩስ ልውውጦች ከተማዋ ከባድ የፀጥታ ሁኔታ ውስጥ ቆይታለች።
እንደ እማኞች ገለፃ የችግሩ መንስዔ ባለፈው ቅዳሜ በአል-ጃባል አካባቢ አንድ የጎሳ ቡድን ሁለት የማሳሊት ጎሳ ተወላጆችን መግደሉ ነው።
የተጎጂዎች ቤተሰቦች እሁድ ዕለት ተሰብስበው ባለሥልጣናት ወንጀለኞቹን በቁጥጥር ስር እንዲያውሉ ቢጠይቁም ይህ ሊሆን አልቻለም ነው የተባለው።
ሌላ ቡድን ደግሞ በተጎጂዎች የቀብር ሥነ ስርዓት ላይ ጥቃት በመፈፀም ሦስተኛ ሰው መግደሉ ሁኔታውን ይበልጥ ማባባሱን እማኞች ገልጸዋል፡፡
ግጭቶች በተከሰቱበት አል-ጂኔይና ከተማ የአል-ጃባል አካባቢ በርካታ ሰዎች የተፈናቀሉ ሲሆን “በአቡዛር የተፈናቃዮች ካምፕ የሚገኙ ቤቶች እና በአካባቢው የሚገኝ የህክምና ማዕከል ተቃጥለዋል” ብለዋል ምስክሮች።
የምዕራብ ዳርፉር አስተዳዳሪ መሃመድ አብደላህ በትናትናው እለት በሰጡት መግለጫ አሁን ላይ አካባቢው መረጋጋቱን እና በሚሊሻዎች መካካል ስደረግ የነበረው የተኩስ ልውውጥ ጋብ ማለቱን አስታውቀዋል።
በንጹሃን ዜጎች ላይ ጥቃት ካደረሱ ሚሊሻዎች ውስጥ የተወሰኑት ዳርፉርን ከሚያዋስኑ ጎረቤት ሀገራት የገቡ መሆናቸውንም አስተዳዳሪው አንስተዋል።
ከድንበር ዘለል ሚሊሻዎች ውስጥ የተወሰኑት ከቻድ እንዲሁም ከሊቢያ የመጡ እንደሚገኙበትም ነው ያስታወቁት።