በሱዳን ምዕራብ ዳርፉር በተነሳ የጎሳ ግጭት የሟቾች ቁጥር 40 ደረሰ
በተፈናቃዮች ካምፕ የሚገኙ መኖሪያ ቤቶች እና በአካባቢው የሚገኙ የህክምና ማዕከላት መቃጠላቸውም ተገልጿል
ከትናንት በስቲያ ጀምሮ በምዕራብ ዳርፉር ግጭቶች መባባሳቸውን የሱዳን ሐኪሞች ኮሚቴ አስታውቋል
በሱዳን የምዕራብ ዳርፉር ግዛት ዋና ከተማ አል-ጂኔይና ትናንት በተከሰተ የጎሳ ግጭት 40 ሰዎች ሲሞቱ ከ50 በላይ ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ገልጿል፡፡
ግጭቱ የተከሰተው በአካባቢው በሚኖሩ የአረብ ጎሳ እና አረብ ባልሆኑ ማህበረሰቦች መካከል መከሰቱ የተገለጸ ሲሆን በከተማዋ የሚኖሩ ከ700 ሺህ በላይ ነዋሪዎች በግጭቱ እንቅስቃሴያቸው ታውኳል ተብሏል።
የአይን እማኞች ለአል ዐይን ዜና እንደገለጹት ፣ በአከባቢው ቤቶችን ማቃጠልን ጨምሮ በሁለት ጎሳዎች መካከል በሚደረጉ የተኩስ ልውውጦች ከተማዋ ከባድ የፀጥታ ሁኔታ ላይ ትገኛለች፡፡
እንደ እማኞች ገለፃ የችግሩ መንስዔ ባለፈው ቅዳሜ በአል-ጃባል አካባቢ አንድ የጎሳ ቡድን ሁለት የማሳሊት ጎሳ ተወላጆችን ሰዎችን መግደሉ ነው፡፡
የተጎጂዎች ቤተሰቦች እሁድ ዕለት ተሰብስበው ባለሥልጣናት ወንጀለኞቹን በቁጥጥር ስር እንዲያውሉ ቢጠይቁም ይህ ሊሆን አልቻለም ነው የተባለው፡፡
ሌላ ቡድን ደግሞ በተጎጂዎች የቀብር ሥነ ስርዓት ላይ ጥቃት በመፈፀም ሦስተኛ ሰው መግደሉ ሁኔታውን ይበልጥ ማባባሱን እማኞች ገልጸዋል፡፡ ይህን ተከትሎ ትናንት መለስተኛ ግጭቶች ተፈጥረው ፣ በዛሬው ዕለት ደግሞ ግጭቱ ተባብሶ የሰዎችን ህይወት መቅጠፉንም ተናግረዋል፡፡
ግጭቶች በተከሰቱበት አል-ጂኔይና ከተማ የአል-ጃባል አካባቢ በርካታ ሰዎች የተፈናቀሉ ሲሆን “በአቡዛር የተፈናቃዮች ካምፕ የሚገኙ ቤቶች እና በአካባቢው የሚገኝ የህክምና ማዕከል ተቃጥለዋል” ብለዋል ምስክሮች፡፡
የሱዳን ሐኪሞች ኮሚቴ የምዕራብ ዳርፉር ቅርንጫፍ በበኩሉ በሰጠው መግለጫ “የምዕራብ ዳርፉር ዋና ከተማ በሆነችው አል-ጂኔይና ከተማ እንደ አዲስ ግጭት የተከሰተ ሲሆን ከእሑድ ማለዳ ጀምሮም የበለጠ ተስፋፍቷል” ብሏል፡፡
በአል-ጂኔይና ከተማ በሚገኙ የተለያዩ የህክምና ማዕከላት ፣ የህክምና እርዳታ እያገኙ የነበሩ 40 ሰዎች መሞታቸውን እና ከ50 በላይ ሰዎች መቁሰላቸውን ኮሚቴው ማረጋገጡንም ይፋ አድርጓል፡፡
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በአል-ጂኔይና ተደጋጋሚ የጎሳ ግጭቶች ተስተናግደው በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የሞቱ ሲሆን በሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ተፈናቅለዋል፡፡