በሱዳን ምዕራብ ዳርፉር በጎሳ ግጭት 18 ሰዎች ተገደሉ
በተፈናቃዮች ካምፕ የሚገኙ ቤቶች እና በአካባቢው የሚገኝ አንድ የህክምና ማዕከል መቃጠላቸውም ተገልጿል
ከትናንት ጀምሮ በምዕራብ ዳርፉር ግጭቶች መባባሳቸውን የሱዳን ሐኪሞች ኮሚቴ አስታውቋል
በሱዳን የምዕራብ ዳርፉር ግዛት ዋና ከተማ አል-ጂኔይና ዛሬ ሰኞ በተከሰተ የጎሳ ግጭት በትንሹ 18 ሰዎች መሞታቸው እና ብዙዎች መቁሰላቸው ተገልጿል፡፡
የአይን እማኞች ለአል ዐይን ዜና እንደገለጹት ፣ በአከባቢው ቤቶችን ማቃጠልን ጨምሮ በሁለት ጎሳዎች መካከል በሚደረጉ የተኩስ ልውውጦች ከተማዋ ከባድ የፀጥታ ሁኔታ ላይ ትገኛለች፡፡
እንደ እማኞች ገለፃ የችግሩ መንስዔ ባለፈው ቅዳሜ በአል-ጃባል አካባቢ አንድ የጎሳ ቡድን ሁለት የማሳሊት ጎሳ ተወላጆችን ሰዎችን መግደሉ ነው፡፡
የተጎጂዎች ቤተሰቦች እሁድ ዕለት ተሰብስበው ባለሥልጣናት ወንጀለኞቹን በቁጥጥር ስር እንዲያውሉ ቢጠይቁም ይህ ሊሆን አልቻለም ነው የተባለው፡፡
ሌላ ቡድን ደግሞ በተጎጂዎች የቀብር ሥነ ስርዓት ላይ ጥቃት በመፈፀም ሦስተኛ ሰው መግደሉ ሁኔታውን ይበልጥ ማባባሱን እማኞች ገልጸዋል፡፡ ይህን ተከትሎ ትናንት መለስተኛ ግጭቶች ተፈጥረው ፣ በዛሬው ዕለት ደግሞ ግጭቱ ተባብሶ የሰዎችን ህይወት መቅጠፉንም ተናግረዋል፡፡
ግጭቶች በተከሰቱበት አል-ጂኔይና ከተማ የአል-ጃባል አካባቢ በርካታ ሰዎች የተፈናቀሉ ሲሆን “በአቡዛር የተፈናቃዮች ካምፕ የሚገኙ ቤቶች እና በአካባቢው የሚገኝ የህክምና ማዕከል ተቃጥለዋል” ብለዋል ምስክሮች፡፡
የሱዳን ሐኪሞች ኮሚቴ የምዕራብ ዳርፉር ቅርንጫፍ በበኩሉ በሰጠው መግለጫ “የምዕራብ ዳርፉር ዋና ከተማ በሆነችው አል-ጂኔይና ከተማ እንደ አዲስ ግጭት የተከሰተ ሲሆን ከእሑድ ማለዳ ጀምሮም የበለጠ ተስፋፍቷል” ብሏል፡፡
በአል-ጂኔይና ከተማ በሚገኙ የተለያዩ የህክምና ማዕከላት ፣ የህክምና እርዳታ እያገኙ የነበሩ 18 ሰዎች መሞታቸውን እና 54 መቁሰላቸውን ኮሚቴው ማረጋገጡንም ይፋ አድርጓል፡፡
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በአል-ጂኔይና ተደጋጋሚ የጎሳ ግጭቶች ተስተናግደው በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የሞቱ ሲሆን በሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ተፈናቅለዋል፡፡