ጥቃቱ በለጥ ሃዎ በተባለችው የድንበር ከተማ ከትናንት በስቲያ ምሽት የተፈጸመ ነው
ኬንያ አስታጥቃቸዋለች ባለቻቸው እና ድንበር አቋርጣ በገቡ ሚሊሻዎች ጥቃት እንደተፈጸመባት ሶማሊያ አስታወቀች፡፡
ጥቃቱ ከትናንት በስቲያ ምሽት ጌዶ በተባለው ክልል በዋናነትም በለጥ ሃዎ (ቡሉ ሃዎ) አካባቢ የተፈጸመ ነው፡፡
በለጥ ሃዎ ሶማሊያ ከሶማሊ ላንድ በምትዋሰንበት ድንበር ላይ የምትገኝ ከተማ ናት፡፡
“በኬንያ የተቀነባበረውን ይህን ህገ ወጥ ወረራ የሶማሊያ ጦር በብቃት መክቶታል” ብሏል የሶማሊያ መንግስት ጉዳዩን በማስመልከት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ በኩል ባወጣው መግለጫ፡፡
ድርጊቱን በጥብቅ እንደሚያወግዝም አስታውቋል፡
“ከአብሮ መኖር እና ከዓለም አቀፍ የመከባር መርሆዎች፣ ከግዛታዊ አንድነት እና ሉዓላዊነት የሚጻረር ነው” ሲልም ነው የገለጸው፡፡
ወደፊት በጉዳዩ ላይ ዝርዝር መረጃዎችን እንደሚሰጥም አስታውቋል፡፡
በጥቃቱ የደረሰ ጉዳት ይኑር አይኑር የተገለጸ ነገር የለም፡፡
ኬንያም ብትሆን እስካሁን በጉዳዩ ላይ የሰጠችው ምላሽ የለም፡፡ ከአሁን በፊት ግን በአካባቢው ሰላም እንዲወርድ ያላትን ፍላጎት ስትገልጽ ነበረ፡፡
ጎብጆግ የተሰኘው የዜና ምንጭ ግን የበለጥ ሃዎ ምክትል ፖሊስ ኮሚሽነርን ጨምሮ 5 ህጻናት መገደላቸውን ዘግቧል፡፡
ምክትል ፖሊስ ኮሚሽነር መሃመድ አብዲ ኑር ከሁለት ጠባቂዎቻቸው ጋር በመሆን ውጊያ ውስጥ ነበሩ ነው ያለው ጎብጆግ፡፡
ሶማሊያ ጉዳዩን ወደ አፍሪካ ህብረት መውሰዷንም ነው የዘገበው፡፡
ጎብጆግ የኬንያን ዝምታ “ፕሬዝዳንት ሞሃመድ አብዱላሂ ፋርማጆ አጋጣሚውን ለፖለቲካ ፍጆታ ለመጠቀም ያላቸውን ፍላጎት በመረዳቷ ነው ሲል” የባለሙያዎችን ሃሳብ ዋቢ አድርጎ ያስቀምጣል፡፡
ብሄራዊው የሶማሊያ የቴሌቪዥን ጣቢያ ሚሊሻዎቹ ሙሉ በሙሉ መደምሰሳቸውን የሃሪቱን ጦር ዋቢ አድርጎ ዘግቧል፡፡
በጉዳዩ ላይ መግለጫን የሰጡት የምድር ጦር አዛዡ ብርጋዲዬር ጄነራል መሃመድ ታሃሊልም ይህንኑ ብለዋል፡፡
በግዛቱ ታጥቀው ይንቀሳቀሱ የነበሩ መቶ ሚሊሻዎች መያዛቸውንም ነው አዛዡ የተናገሩት፡፡
ሶማሊያ እና ኬንያ ከቅርብ ወራት ወዲህ በሻከረ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ውስጥ ይገኛሉ፡፡
በውስጥ ጉዳዮቼ ጣልቃ ገብታለች በሚል የከሰሰችው ሶማሊያ ሞቃዲሾ የነበረውን የኬንያ አምባሳደር ጠርታ ማብራሪያ እስከመጠየቅ ከዚያም አለፍ ሲል ናይሮቢ የሚገኘውን ኤምባሲዋን እስከመዝጋት መድረሷ የሚታወስ ነው፡፡