“ኡሑሩ ኬንያታን የቴሌኮም ፍቃድ ስምምነትን በምንፈራረምበት በዛሬው ታሪካዊ ዕለት ወደ ኢትዮጵያ እንኳን ደኅና መጡ ለማለት እወዳለሁ”- ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ
የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ዛሬ ለአንድ ቀን ይፋዊ የስራ ጉብኝት በሚል አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ ቀደም ብለው ኢትዮጵያ በደረሱት በሃገራቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ራይቼል ኦማሞ ታጅበው የመረጃ እና ኮሙኒኬሽን ሚኒስትራቸውን ጆ ሙሼሩን አስከትለው ነው አዲስ አበባ የገቡት፡፡
ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በደረሱ ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ተቀብለዋቸዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ኡሁሩ “ታሪካዊ” ባሉትና የቴሌኮም ፍቃድ ስምምነት በሚፈረምበት ዕለት መምጣታቸውን ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ በይፋዊ የማህበረሰብ ገጾቻቸው አስታውቀዋል፡፡
የፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤትም ይህንኑ ገልጿል፡፡
የኬንያው የቴሌኮም ኩባንያ ሳፋሪ ኮም የሚመራው የአራት የደቡብ አፍሪካ፣ ብሪታኒያ እና የጃፓን የቴሌኮም ኩባንያዎች ስብስብ ‘የግሎባል ፓርትነርሽፕ ፎር ኢትዮጵያ’ በኢትዮጵያ በቴሌኮም ኦፕሬተርነት ዘርፍ ለመሳተፍ የወጣውን ጨረታ ማሸነፉ ይታወሳል፡፡
በሳፋሪ ኮም የሚመራው ስብስቡ ቮዳፎንን፣ ቮዳኮምንና ሱሚቶሞን ያካተተ ነው፡፡
ስብስቡ የማሸነፊያ ዋጋውን 850 ሚሊዬን ዶላር ለመንግስት ገቢ አደረገ መባሉም አይዘነጋም፡፡
ጉብኝቱ ከፊርማ ስነ ስርዓቱ ያለፈ ምን አንድምታ አለው?
ኢትዮጵያ እና ኬንያ ዘመናት ያቆጠረ ከሁለትዮሽም ያለፈ ግንኙነት አላቸው፡፡ ግንኙነቱ ይፋዊ የዲፕሎማሲያዊ መልክ የያዘው ኢትዮጵያ በኬንያ ቆንስላ ከከፈተችበት እ.ኤ.አ ከ1954 የሚጀምር ነው፡፡
በመቀጠልም ኢትዮጵያ በ1961 የመጀመሪያውን አምባሳደር ወደ ኬኒያ የላከች ሲሆን ኬኒያ ደግሞ በ1967 ኤምባሲዋን በአዲስ አበባ ከፍታለች እንደ ኢዜአ የዛሬ ዘገባ።
ከዚያም ወዲህ ሁለቱ ሃገራት በተለያዩ ሃገራዊ እና ቀጣናዊ ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ዙሪያ ጭምር በጋራ ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡
በተለይ እስከ ቀጣናዊ የምጣኔ ሃብት ውህደት ሊያደርስ የሚችል ግንኙነትን እናደርጋለን በሚል ከተነገረበት ከባለፉት ሶስት ዓመታት ወዲህ ግንኙነቱ ይበልጥ ጠንክሮ ነበር፡፡
ይህን ተከትሎ ኡሁሩ ኬንያታ በደብረ ብርሃን ኢንዱስትሪ ፓርክ የምረቃ ስነ ስርዓት ላይ በክብር እንግድነት ጭምር ተገኝተው እንደነበር ይታወቃል፡፡
ሆኖም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግንኙነቱ በመጠኑም ቢሆን መላላቶች እንደተስተዋሉበት ይነገራል፡፡
ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ጋር በምታደርገው ግንኙነት ኬንያ ደስተኛ አይደለችምም ነው አንዳንድ የቀጣናው ተንታኞች የሚሉት፡፡
የሃገራቱ ግንኙነት እንደ ወትሮው እየሆነ አይደለም በሚል የሚናገሩም አሉ፡፡
በትግራይ ክልል ጉዳይ ኢትዮጵያ አጀንዳ ሆና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በቀረበችበት ጊዜ የምክር ቤቱ ተለዋጭ አባል የሆነችው ኬንያ ኢትዮጵያን ሳትደግፍ መቅረቷንም እንደማሳያ ያነሳሉ፡፡
በጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ እና በፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የተመረቀው የሞያሌ የጋራ ፍተሻ ጣቢያም ከምረቃ በኋላ አንዲትንም አገልግሎት ሳይሰጥ ከ7 የማያንሱ ወራትን አስቆጥሯል፡፡
ጣቢያው የሃገራቱን የወጪ ገቢ ንግድ ማቀላጠፊያ ሆኖ እንደሚያገለግልና በቶሎ ስራ እንደሚጀምር ነበር በወቅቱ ሲነገር የነበረው፡፡
የዛሬው የፕሬዝዳንት ኡሁሩ ጉብኝት መጠነኛ መቀዛቀዝ የተስተዋለበትን ይህን ግንኙነት የበለጠ ለማነቃቃት እና በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ተቀራርቦ ለመስራት የሚቻልበትን አጋጣሚ ለመፍጠር እንደሚያስችል ይጠበቃል፡፡