ጀርመን ጨምሮ ከ14 በላይ የአውሮፓ ሀገራት ከሚሳኤል ጥቃት ራሳቸውን ለመከላከል ህብረት ፈጠሩ
ሀገራቱ ከሩሲያ ሊሰነዘር የሚችል የሚሳኤል ጥቃት ሊኖር እንደሞችል ስጋት እንዳላቸው ገልጸዋል
ሀገራቱ ገንዘብ በጋራ በማዋጣት የአየር ጥቃትን የሚከላከል የጦር መሳሪያ ለመግዛትም ተስማምተዋል
ጀርመን ጨምሮ ከ14 በላይ የአውሮፓ ሀገራት ከሚሳኤል ጥቃት ራሳቸውን ለመከላከል ህብረት ፈጠሩ።
ስምንት ወራት ሊሞላው ጥቂት ቀናት የቀሩት የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት በየጊዜው አዳዲስ ክስተቶች ማስተናገዱን ቀጥሏል።
የዓለም ምግብ እና ነዳጅ ዋጋ መናር፣ አራት የዩክሬን ግዛቶች በህዝበ ውሳኔ ወደ ሩሲያ መጠቃለል፣ አዲስ የዲፕሎማሲ ህብረት እና ሌሎችም ክስተቶች ከጦርነቱ ውጤቶች መካከል ዋነኞቹ ናቸው።
ባሳለፍነው ቅዳሜ ክሪሚያን ከሌሎች የሩሲያ ግዛቶች ጋር የሚያስተሳስረው ድልድይ በዩክሬን አደጋ ደርሶበታል ያለችው ሩሲያ በዩክሬን ከተሞችን ላይ የሚሳኤል ጥቃት በመሰንዘር ላይ ትገኛለች።
የሩሲያን አዲስ ጥቃት ተከትሎም ከ14 በላይ ሀገራት ከተሞቻቸውን በጋራ ከሚሳኤል ጥቃት ለሙከላከል አዲስ ህብረት መፍጠራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
ጀርመን፣ ቤልጂየም፣ ብሪታንያ፣ ቡልጋሪያ፣ ኖርዌይ፣ ቼክ ሪፐብሊክ፣ ኢስቶኒያ፣ ሆላንድ፣ ስሎቫኪያ፣ ሮማንያ፣ እና ፊንላንድ ህብረቱን ከፈጠሩ የአውሮፓ ሀገራት መካከል ዋነኞቹ ናቸው።
ይሄንን ህብረት ጀርመን እንደምትመራው የተገለጸ ሲሆን፤ ወጪን በቀነሰ መንገድ ባጋራ የአየር ላይ ጥቃቶችን ሊያስቆም የሚችሉ የጦር መሳሪያዎችን በሙግዛት በአውሮፓ ከተሞች ላይ ሊፈጠር የሚችልን ጥቃት ለመመከት ያለመ ነው ተብሏል።
ሀገራቱ ከተሞቻቸውን ከሚሳኤል ጥቃት ለመጠበቅም ጀርመን እና እስራኤል ሰራሽ የአየር ጥቃት ማምከኛ የጦር መሳሪያዎችን ጥቅም ላይ እንደሚያውሉም ተገልጿል።
አዲስ ህብረት የፈጠሩት እነዚህ ሀገራት አብዛኞቹ የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ጦር ወይም ኔቶ አባል ሀገራት ሲሆኑ አዲሱ ጥምረት ከዚህ በተጨማሪ እና በተናበበ መንገድ ይሆናልም ተብሏል።