ሩሲያ የዩክሬንን ጦርነት ካሸነፈች አውሮፓ ስጋት ውስጥ እንደሚወድቅ ኔቶ ገለጸ
የኔቶ አባል ሀገራት ራሳቸውን ስጋት ውስጥ በማይጥል መንገድ ዩክሬንን እንዲደግፉም አሳስቧል
የባልቲክ አካባቢ ሀገራት ከሌሎች ሀገራት በበለጠ የጦር መሳሪያ ለዩክሬን ድጋፍ አድርገዋል ተብሏል
ሩሲያ የዩክሬንን ጦርነት ካሸነፈች አውሮፓ ስጋት ውስጥ እንደሚወድቅ ኔቶ ገለጸ።
ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ጦርን እቀላቀላሉሁ ማለቷን ተከትሎ ከሩሲያ ጋር ወደ ጦርነት ከገባች ሰባት ወራትን አስቆጥሯል።
ባለፉት ሰባት ወራት ውስጥም በዚህ ጦርነት ምክንያት ብዙ ክስተቶች የተፈጠሩ ሲሆን ከዓለም ምግብና ነዳጅ ከመጨመር በተጨማሪ አራት የዩክሬን ግዛቶች በህዝበ ውሳኔ ወደ ሩሲያ ተጠቃለዋል።
ባሳለፍነው ቅዳሜ ክሪሚያን ከተቀረው ሩሲያ ጋር የሚያስተሳስረው ድልድይ በዩክሬን እንደተመታባት የገለጸችው ሩሲያ የዩክሬን ዋና ዋና ከተሞችን በሚሳኤል መደብደቧን እንደቀተለች ሮይተርስ ዘግቧል።
የሩሲያ ሚሳኤል በተለይም የዩክሬን ዋና ከተማ የሆነችው ኪቭን ደጋግሞ መምታቱን ተከትሎ በከተማዋ ውጥረት የነገሰ ሲሆን ባቡርን ጨምሮ በርካታ አገልግሎቶች ተቋርጠዋል ተብሏል።
ይሄንን ተከትሎም የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ጦር ወይም ኔቶ ዋና ጸሀፊ ጄንስ ስቶልትንበርግ ሩሲያ ጦርነቱን ልታሸንፍ አይገባም ብለዋል።
ዩክሬን ከሩሲያ ጋር የጀመረችውን ጦርነት እንድታሸንፍ የአውሮፓ ሀገራት እስከመጨረሻው ድረስ ድጋፍ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል።
አሜሪካንን ጨምሮ በርካታ የአውሮፓ ሀገራት ለዩክሬን የጦር መሳሪያ ድጋፍ እያደረጉ ቢሆንም ሀገራቱ ብሔራዊ መጠባበቂያ ጦራቸውን ለአደጋ በማያጋልጥ መንገድ ሊሆን ይገባልም ብለዋል።
የባልቲክ ሀገራት ከሌሎች የኔቶ አባል ሀገራት ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ መጠን ያለው የጦር መሳሪያ ድጋፍ እንዳደረጉ ተገልጿል።
በተለይም ለዩክሬን ጎረቤት የሆኑት ላቲቪያ፣ ኢስቶኒያ እና ፖላንድ ከዓመታዊ ምርት መጠናቸው ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ ለዩክሬን ረድተዋል ተብሏል።
እነዚህ ሀገራት ራሳቸውን ለአደጋ በጣለ መንገድ የጦር መሳሪያ ለዩክሬን መስጠታቸው ለኔቶ ስጋት እንደሚሆን የድርጅቱ ዋና ጸሀፊ ስቶልትንበርግ አክለዋል።
ሩሲያ በዩክሬን የጀመረችውን ጦርነት ካሸነፈች አውሮፓ የበለጠ ለአደጋ እንደሚጋለጥም ተናግረዋል።
ኔቶ የሩሲያን ድርጊት በትኩረት እየተከታተለ መሆኑን የገለጹት ዋና ጸሀፊው ሞስኮ ጦርነቱን በአሸናፊነት እንዳታጠናንቅ ሁሉም የኔቶ አባል ሀገራት ለዩክሬን የሚችሉትን እና ራሳቸውን ለአደጋ በማያጋልጥ መንገድ እንዲደግፉ ጥሪ አቅርበዋል።
የዩክሬን- አፍሪካ ጉባኤ እንዲካሄድ እና አፍሪካዊያን ሩሲያን እንዲያወግዙ ለማድረግ ወደ አፍሪካ ተጉዘው የነበሩት የዩክሬን ውጪ ጉዳይ ሚንስትር ድሚትሮ ኩሌባ ጉብኝታቸውን አቋርጠው ወደ ኬቭ መመለሳቸው ይታቀሳል።