ሩሲያ ዩክሬን ለኔቶ ያቀረበችውን የአባልነት ጥያቄ ብትሰርዝም ጦርነቱን እንደማታቆም ገለጸች
የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ 186ኛው ቀን ላይ ይገኛል
አሜሪካ ለዩክሬን ከ70 ኪሎ ሜትር በላይ የሚጓዝ የጦር መሳሪያ ለዩክሬን ከሰጠች ለሁለቱ ሀገራት ጥሩ እንደማይሆን ተገልጿል
ሩሲያ ዩክሬን ለኔቶ ያቀረበችውን የአባልነት ጥያቄ ብትሰርዝም እንኳ ጦርነቱን እንደማታቆም ገለጸች።
የሩሲያ የቀድሞ ፕሬዝዳንት እና የአሁኑ የሩሲያ ደህንነት ምክትል ኃላፊ ድሚትሪ ሜድቬዴቭ ከፈረንሳይ ቴሌቪዥን ጋር በሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ዙሪያ ቃለመጠይቅ አድርገዋል።
ሜድቬዴቭ በዚህ ጊዜ እንዳሉት ዩክሬን የኔቶ አባል ለመሆን ያቀረበችውን ጥያቄ ብታቋርጥም ሩሲያ ጦርነቱን ትቀጥላለች ብለዋል።
ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት ሩሲያ ከዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዶሚር ዘለንስኪ ጋር ለመወያየት ብትሞክርም አለመሳካቱንም አክለዋል።
የዩክሬን የኔቶ አባልነትን ሩሲያ ፈጽሞ የማትቀበለው ነገር መሆኑን ያነሱት ሜድቬዴቭ፤ ዩክሬን ኔቶን አልቀላቀልም ብትልም በሁለቱ ሀገራት መካከል ሰላምን ለማስፈን በቂ አይደለም ሲሉም ጠቅሰዋል።
በመሆኑም ሩሲያ በዩክሬን የጀመረችው ወታደራዊ ተልዕኮ እስከሚሳካ ድረስ ጦርነቱ ይቀጥላልም ብለዋል።
አሜሪካ ለዩክሬን እየሰጠች ያለችው የጦር መሳሪያዎች እስከ 70 ኪሎ ሜትር ድረስ ጥቃት ማድረስ የሚያስችሉ ናቸው፣ ከዛ ባለፈ ግን ወደ ሩሲያ ድንበር የሚዘልቁ የጦር መሳሪያዎችን ከሰጠች ግን ለሩሲያ ስጋት ስለሚሆን ለሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ጥሩ እንደማይሆን ሜድቬዴቭ አክለዋል።
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከሩሲያ ጋር ቀጥታ ጦርነት ውስጥ ላለችው ዩክሬን ተጨማሪ የሶስት ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ያላቸው የጦር መሳሪያ ድጋፍ ከሰሞኑ መፈረማቸው ይታወሳል።
አሜሪካ የጦር መሳሪያውን ድጋፍ ያደረገችው ዩክሬን የኑክሌር ጥቃት ከሩሲያ ሊያጋጥማት ይችላል በሚል እንደሆነ ሮይተርስ ዘግቧል።
የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ 186ኛ ቀኑ ላይ ሲገኝ ከ10 ሚሊዮን በላይ ዩክሬናዊያን ወደ ጎረቤት ሀገራት ተሰደዋል።