በአፍሪካ በግጭት ምክንያት ከ 14 ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸውን ጥናት አመላከተ
ትምህርት ቤቶቹ የተዘጉት ግጭት ባለባቸው 24 የአፍሪካ ሀገራት ነው
በዚህ ችግር ምክንያት በሚሊየን የሚቆጠሩ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ ሆነዋል
በአፍሪካ በሚገኙ ግጭቶች 14300 ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸውን ጥናት አመላክቷል፡፡
ይህ ቁጥር በ2023 ከነበረው ጋር ሲወዳደር የአንድ ሺህ ጭማሪ አሳይቷል
የትጥቅ ግጭቶች በሚገኙባቸው 24 ሀገራት በሚሊየን የሚቆጠሩ ተማሪዎች ከትምህርት ውጭ ሆነዋል የሚለው ጥናቱ ቡርኪናፋሶ ፣ ናይጄሪያ ፣ ካሜሮን ቻድ እና ኒጄር በርካታ ትምህርት ቤቶች ከተዘጉባቸው መካከል እንደሚገኙ ጠቅሷል፡፡
የኖርዌይ የስደተኞች ካውንስል ባጠናው ጥናት እስከ 2024 ሀምሌ ወር ድረስ በዚህ ችግር የተነሳ 2.8 ሚሊየን ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ መሆናቸውን ነው ያመላከተው፡፡
በሀገራቱ እየተስፋፉ በሚገኙት ግጭቶች ወንድ ተማሪዎች ታጣቂ ቡድኖችን ሲቀላቀሉ ሴቶች ደግሞ ያለ እድሜያቸው እንዲዳሩ ምክንያት ሆነዋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት የህጻናት አድን ድርጅት (ዩኒሴፍን) ጨምሮ ሌሎች የእርዳታ ድርጅቶች ህጻናቱ ተጣቂ ቡድኖችን እንዳይቀላቀሉ የተለያዩ የኢመደበኛ ትምህርቶችን እንዲያገኙ እና ለወላጆቻቸው ድጋፍ እያደረጉ ቢገኝም እምብዛም ለውጥ እንዳላመጣ የአሜሪካ ድምጽ ዘግቧል፡፡
የጉልበት ብዝበዛ ሌላው አሳሳቢ ችግር ነው ጦርነት በፈጠረው ተጽዕኖ በቀደመው ልክ እራሳቸውን መደጎም የተሳናቸው ቤተሰቦች ልጆችን ያለ እድሜያቸው ወደ ስራ እያሰማሯቸው ይገኛሉ፡፡
ከዚህ ባለፈም በጦርነት ስነልቦና ውስጥ ለረጅም ጊዜ የሚቆዩ ህጻናት ወደ ትምህርት ገበታቸው ለመመለስ ያላቸው ፍላጎት እንዲሁም አዕምሯቸው ትምህርት ለመቀበል ያለው ዝግጁነት እጅግ ዝቅተኛ ነው የተባለው፡፡
ከሁለት አመታት በላይ በግጭት ውስጥ በምትገኝው ዴሞክራሲያዊት ኮንጎ 1450 ትምህርት ቤቶች የተዘጉ ሲሆን 500 ሺህ ተማሪዎች ከትምህርታቸው ተስተጓጉለዋል፡፡
ትምህርት ቤቶቹ የሚዘጉባቸው ምክንያቶች ከቦታ ቦታ የተለያየ ቢሆንም በታጣቂዎች ዘንድ በመንግስታዊ ተቋምነት መታየታቸው እንዲሁም ለጦር ካምፕነት አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸው ከዋና ምክንያቶች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡
የኖርዌይ የስደተኞች ካውንስል መንግሰት እና ታጣቂዎች የህጻናትን ከጥቃት የመጠበቅ መብታቸውን እንዲያከብሩ እና ትምህርት ቤቶችን ከጥቃት ኢላማነት እንዲያስወጡ ጠይቋል፡፡