በኢትዮጵያና ሶማሊያ ዲፕሎማሲያዊ ውጥረት ዙሪያ የአሜሪካ አቋም ምንድን ነው?
በሶማሊያ የአሜሪካ አምባሳደር ኢትዮጵያና ሶማሊያ ወደ ግጭት ከሚያስገቡ ጸብ አጫሪ ድርጊቶች እንዲታቀቡ አሳስበዋል
አምባሳደሩ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ የሚገኙበትን ዲፕሎማሲያዊ ውጥረት በሰላም እንዲፈቱ አሜሪካ ድጋፍ እንደምታደርግ ገልጸዋል
ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ የሚገኙበትን ዲፕሎማሲያዊ ውጥረት በሰላም እንዲፈቱ አሜሪካ ድጋፍ እንደምታደርግ በሶማሊያ የአሜሪካ አምባሳደር ሪቻርድ ራይሊ አስታውቀዋል።
አምባሳደሩ ከአሜሪካ ድምፅ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ በኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ መካከል የተፈረመውን የወደብ የመግባብያ ስምምነት አሜሪካ እውቅና እንደማትሰጥም አስታውቀዋል።
አምባሳደር ሪቻርድ ራይሊ ክደብ ስምምነቱ ጋር በተያያዘ በሶማሊያ እና በኢትዮጵያ መካከል የተፈጠረው አለመግባባት ዲፕሎማሲያዊ እልባት እንዲያገኝ አሳስበዋል።
አዲስ አበባ እና ሞቃዲሾ የሚገኙበትን ውጥረት ለመፍታት እንዲሁም ሰላማዊ አመራጮችን ለማፈላለግ ሀገራቸው ድጋፍ እንደምታደርግም ገልጸዋል።
በተጨማሪም ሁለቱ ሀገራት ወደ ግጭት ከሚያስገቡ ጸብ አጫሪ ድርጊቶች መታቀብ እንደሚኖርባቸው፣ አሜሪካ እና አለም አቀፉ ማህበረሰብ ችግሩን በአፋጣኝ ለመፍታት የጋራ ጥረት ለማድረግ እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውንም አመላክተዋል።
ባሰለፍነው አመት በሀርጌሳ እና አዲስ አበባ መከከል የተፈረመውን የወደብ ስምምነት ተከትሎ በቀጠናው ከፍ ያለ ውጥረት መንገሱ ይታወቃል።
ስምምነቱ ሉላዊነቴን አንደመጣስ ነው ያለችው ሶማሊያ በቱርክ አደራዳሪነት ሁለት ጊዜ በአንካራ ከኢትዮጵያ መንግሰት ጋርያለ ስምምነት የተጠናቀቀ ድርድር አካሂዳለች።
ሀገራቱ ከአራት ቀናት በኋላ በፈረንጆቹ መስከረም 17 በመጪው ማክሰኞ ሶስተኛ ዙር ድርድራቸውን ያካሂዳሉ።
በድርድሩ ሶማሊያን ወክለው እየተደራደሩ ከሚገኙ ልኡካን መካከል አንዱ የሆኑት የሶማሊያ የፕላን አለም አቀፍ ትብብር ሚንስትር አብዲ አያንቲ ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የደረሰችውን ስምምነት እስካልሰረዘች ድረስ ከድርድሮቹ ውጤት መጠበቅ አይቻልም ብለዋል።
ከቪኦኤ ጋር ቆይታ ያደረጉት የዋሽንግተን የስታረቴጂክ አለምቀፋዊ ግንኙነት ጥናት ማዕከል ተመራማሪው ካሜሮን ሀድሰን አሜሪካ ከፍተኛ ውጥረት በሚገኝበት ቀጠና ውስጥ አዲስ የተፈጠረውን ውዝግብ ለማርገብ ዲፕሎማሲያዊ ጫናዎችን ማድረግ እንደሚኖርባት ተናግረዋል።
በተያያዘ ዜና በሶማሊያ የአሜሪካ አምባሳደር ሪቻርድ ራይሊ፤ አሜሪካ ለሶማሊያ የምታደርገውን የደህንነት እና የዲፕሎማሲ ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል ገልጸዋል።
ሶማሊያ የምትገኝበትን የጸጥታ ስጋት እልባት ለመስጠት ዋሽንግተን የምታደርገውን ድጋፍ እንደምታጠናክር አምባሳደር ሪቻርድ ራይሊ ተናግረዋል።
ባለፉት አመታት አሜሪካ ሶማሊያ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት ለምታደርገው ጥረት በ10 ቢሊየን ዶላር የሚቆጠር የጦር መሳርያ እና የደህንነት ድጋፍ ማድረጓን አስታውሰው ድጋፉ በቀጣይ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በተጨማሪም በሞቃዲሾ ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን እንዲሁም ሀገሪቱ በአለም አቀፍ ገበያ ተሳታፊ እንድትሆን እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን እንዲኖራት እገዛ እንደሚደረግ ነው የተናገሩት።