የአለማችን ረጅሟ ሴት በእናቷ ማህጸን እያለች የአለም ክብረወሰን መስበሯን ያውቃሉ?
ቱርካዊቷ ሩሜይሳ ገልጊ ስምንት የአለም ሪከርዶችን በስሟ አስመዝግባለች
የ28 አመቷ ወጣት በ2025 ሀገራትን የመጎብኘት እቅድ እንዳላት ተናግራለች
የአለማችን ረጅሟ ሴት ትናንት 28ኛ አመት ልደቷን አክብራለች።
ቱርካዊቷ ሩሜይሳ ገልጊ በ2 ሜትር ከ15.16 ሴንቲሜትር ቁመት በአለም ድንቃድንቅ መዝገብ ላይ ስሟን ያሰፈረችው ከአስር አመት በፊት ነበር።
በወቅቱ የአለማችን ረጅሟ ታዳጊ ተብላ ስትመዘገብ ቁመቷ ከአሁኑ በሁለት ሴንቲሜትሮች ያንስ እንደነበር የአለም ድንቃድንቅ መዝገብ ያወሳል።
የኮምፒውተር ባለሙያዋ ከ2014 በኋላ ስምንት የአለም ክብረወሰኖችን በስሟ አስመዝግባለች። ሩሜይሳ ከያዘቻቸው ክብረወሰኖች መካከል፦
- በህይወት ያለ ሰው ረጅም ጣት (ሴት) - 11.2 ሴንቲሜትር
- በህይወት ያለ ሰው ሰፊ የእጅ መዳፍ (ሴት) - 22.6 ሴንቲሜትር
- በህይወት ያለ ሰው ረጅም እጆች (ሴት) - ቀኝ እጇ 24.93 ሴንቲሜትር፤ ግራ እጇ 24.26 ሴንቲሜትር
- በህይወት ያለ ሰው ረጅም ጀርባ (ሴት - 55.9 ሴንቲሜትር
ሰባተኛ እና ስምንተኛ ክብረወሰኖችን የያዘችው የአለማችን ረጅሟ ህጻን መሆኗ ባለፈው አመት በጥናት ከተረጋገጠ በኋላ ነው። ሩሜይሳ በፈረንጆቹ ጥር 1 1997 ስትወለድ 59 ሴንቲሜትር ትረዝም ነበር ተብሏል። በዚህም የአለማችን ረጅሟ ጨቅላ ህጻን (ሴት) ክብረወሰንን በመያዝ ስሟ ከእናቷ ሳፊየ ሳሂን ገልጊ ጋር በድንቃድንቅ መዝገብ ላይ ሰፍሯል።
ቱርካዊቷ ቁመተ ሎጋ 9.58 ሴንቲሜትር ርዝመት ያለው ጆሮዋም ሪከርድ ሰብሮ ተመዝግቧል። ሩሜይሳ "ጆሮዬ በጣም ትልቅ ከመሆኑ የተነሳ ሰዎች በተደጋጋሚ በጆሮዬ ሊያሸማቅቁኝ ይሞክሩ ነበር፤ ይህን ክብረወሰን ለመያዝ ያነሳሳኝም ይሄው ነው" ብላ ተናግራ ነበር።
ጆሮዋን በቀዶ ጥገና እንድትቀንስ ምክሮች ቢበዙም አሻፈረኝ ማለቷም የአለም ድንቃድንቅ ክብረወሰኖቿን ቁጥር ስምንት ከማድረሱ በላይ በተፈጥሮ መኩራትን አሳይታለች በሚል አድናቆት እንዲቸራት አድርጓል።
የአለማችን ረጅሟ ሴት የ2025 እቅዷ አለም እየተዟዟሩ መጎብኘት ነው።
ሩሜይሳ ለመጀመሪያ ጊዜ ከሀገሯ ቱርክ የወጣችው ከሁለት አመት በፊት ነበር፤ በአሜሪካ የአለም ድንቃድንቅ መዝገብ ለሚሰራላት ዘጋቢ ፊልም ለመቀረጽ።
በህዳር ወር 2024 የአለም ድንቃድንቅ መዝገብ 20ኛ አመቱን ሲያከብር በእንግሊዝ የተገኘችበት አጋጣሚም ከሀገሯ የወጣችበት ሁለተኛውና የመጨረሻው ጉዞ ነበር። በዚህ ጉዞም ከአለማችን አጭሯ ሴት ዮቲ አምጌ (62.8 ሴንቲሜትር) ጋር መገናኘቷ የሚታወስ ነው።
የስምንት የአለም ክብረወሰኖች ባለቤቷ ሩሜይሳ ገልጊ ቁመቷ ለጉዞ ፈታኝ ሊሆንባት ቢችልም በ2025 በርካታ ሀገራትን የመጎብኘት እቅድ እንዳላት ለአለም ድንቃድንቅ መዝገብ ድረገጽ ተናግራለች።