የ140 ሺህ ዶላር የፕላስቲክ ቀዶ ጥገና “የምመኘውን ህይወት ሰጥቶኛል” የምትለው ጃፓናዊት
ለረጅም ጊዜ ቆጥባ የተሰራቸው ቀዶ ጥገና በማህበራዊ ትስስር ገጽ ከ2 ሚሊየን በላይ ተከታዮችን አስገኝቶላታል
ወጣቷ በቴሌቪዥን ጣቢያዎች ጭምር በመቅረብ ለፕላስቲክ ቀዶ ጥገና ተሟጋች ሆናለች ተብሏል
የፕላስቲክ ቀዶ ጥገና ለበርካቶች እንደ አዲስ ትንሳኤ የሚቆጠር ትሩፋት አስገኝቷል።
በሺህ የሚቆጠር ዶላር አውጥተው ከቀደመው የባሰ ገጽታን ያላበሳቸው ቁጥርም ቀላል አይደለም።
ሂራሴ ኢሪ የተባለችው ጃፓናዊት ግን በፕላስቲክ ቀዶ ጥገና ሙሉ በሙሉ ህይወቴ ተቀየረ ባይ ነች።
የወጣቷን የቅድመ እና ድህረ ቀዶ ጥገና ፎቶዎች ቢመለከቱ ሁለት የተለያዩ ሰዎች ናቸው ማለትዎ አይቀርም።
ሂራሴ ኢሪ የቀዶ ጥገናውን ባላደርግ አሁን የምሰራውን ቅንጡ ስራም ሆነ እውቅና ባላገኘሁ ነበር ስትል ትናግራለች።
አዲስ ገጽታ ያላበሳት የፕላስቲክ ቀዶ ጥገና “የምመኘውን አይነት ስራ አስገኝቶልኛል” የምትለው ወጣቷ፥ በቴሌቪዥን ጣቢያዎች እየቀረበችም የፕላስቲክ ቀዶ ጥገናን ፋይዳ አስረጂ ከሆነች ዋል አደር ብላለች።
ኢሪ በመልኳ ምክንያት ከልጅነቷ ጀምሮ የሚደርስባት መገለልና ስድብ በስነልቦናዋ ላይ ተጽዕኖው በርትቶ ትምህርቷን ከሁለተኛ ደረጃ በላይ እንዳትገፋበት እስከማድረግ ደርሷል።
በዚህም ምክንያት ከፍ ያለ ገንዘብ የሚያስከፍል ስራ ያጣቸው ኢሪ ጉልበት የሚጠይቁ ስራዎችን በመከወን የምታገኘውን ገንዘብ ከምበላው ይቅርብኝ እያለች ስታጠራቅም መቆየቷን አውስታለች።
ለአመታት ያጠራቀመችውን 20 ሚሊየን የን (140 ሺህ ዶላር) ይዛም ወደ ፕላስቲክ ቀዶ ጥገና ሰሪዎች በማምራት ስትሸማቀቅበት የቆየችውን የፊት ገጽታዋን እንዲስተካከል አድርጋለች።
በዚህም የኢሪ ህይወት ሙሉ በሙሉ ተለውጦ የቡጢ ፍልሚያዎችን የማስተዋወቅና ሌሎች ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኙ ስራዎችን ማግኘቷን መግለጿን ነው ኦዲቲ ሴንትራል ያስነበበው።
በማህበራዊ ትስስር ገጿ ከ2 ሚሊየን በላይ ተከታዮችን በማፍራትም ገቢዋን የሚያሳድጉ ስራዎችን እንድትከውን ቀዶ ጥገናው ትልቅ ድርሻ እንዳለው ገልጻለች።
የፕላስቲክ ቀዶ ጥገና ገንዘብን ከማጥፋት ውጭ የረባ ለውጥ አያመጣም ለሚሉ አካላትም በታዋቂ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ላይ በመቅረብ “እኔ ምስክር ነኝ” እያለች ነው።