ፊቷን ለማሳመር 100 ሺህ ዶላር ለፕላስቲክ ቀዶ ህክምና ያወጣችው ጃፓናዊት
አታምሪም የሚሉ አስተያየቶችን ከጓደኞቿ መስማቷ ህክምናውን እንዳደርግ ገፊ ምክንያቴ ነው ብላለች
በፕላስቲክ ቀዶ ህክምና ምክንያት ብዙ ስቃዮችን እንዳሳለፈችም ተናግራለች
ቶዶሮኪ ቻን የምትባለው ጃፓናዊት ከ18 ዓመቷ ጀምሮ የፕላስቲክ ቀዶ ህክምና ስታደርግ ቆይታለች።
አሁን ላይ የ30 ዓመት እድሜ ባለቤት የሖነችው ይህች ጃፓናዊት በትምህርት ቤት እያለች በጓደኞቿ ዘንድ አስቀያሚ መልክ እንዳለኝ ይነግሩኛል ትላለች።
መጀመሪያ ላይ ይህን የጓደኞቿን የአስቀያሚ ነሽ ስድብ ትኩረት ትሰጠው እንዳልነበር የምትናገረው ይህች ጃፓናዊት አስተያየቱ ከትምህርት ቤት ውጪባሉ ሰዎች ጭምር ሲነሳ መልኬን ጠላሁት ብላለች።
በዚህ የተነሳም ቤተሰቦቼን በማሳመን የግድ የፕላስቲክ ቀዶ ህክምና ለማድረግ ወሰንኩ የምትለው ይህች እንስት ከ12 ጊዜ በላይ የቀዶ ህክምናዎችን እንዳደረገች ተናግራለች።
ቶዶሮኪ ሁሉንም የቀዶ ጥገናዎቹን በአይኗ፣ አፍንጫዋ እና ከንፈሯ ላይ እንዳደረገች የተናገረች ሲሆን ለዚህ የህክምና አገልግሎቶችም 13 ሚሊዮን የጃፓን ዩዋን ወይም 100 ሺህ ዶላር ወጪ ማድረጓን ጠቅሳለች።
በጃፓን የፕላስቲክ ቀዶ ህክምና ታዋቂ እየሆነ የመጣ ሲሆን ስለ ህክምናው ጉዳት ብዙ አለመወራቱ ብዙዎች የፕላስቲክ ቀዶ ህክምና ለማድረግ ይነሳሳሉም ብላለች።
ከፕላስቲክ ቀዶ ህክምና ጋር በተያያዘ በጃፓን ብዙሃን መገናኛዎች ላይ በይፋ በመናገር የምትታወቀው ቶዶሮኪ ዝነኛም ሆናለች።
የቀዶ ህክምና በማድረጓ ደስተኛ መሆኗን የምትናገረው ይህች እንስት ብዙ ያልተነገሩ አካላዊ እና ስነ ልቦናዊ ስቃዮችን እንዳሳለፈች ገልጻለች።
ከህክምናው ለማገገም፣ አልፎ አልፎ በሚያጋጥሙ የህክምና ስህተቶች የላይኛው ከንፈሯን እንዳጣች እና ሌሎች ብዙ ስቃዮችን እንዳሳለፈች ከጃፓኑ ታዋቂው ኦሪኮን መጽሄት ጋር በነበራት ቃለ መጠይቅ ላይ ተናግራለች።
ብዙ ወጣቶች የፕላስቲክ ቀዶ ህክምና ለማድረግ የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርጉ እየታዘብኩ ነው የምትለው ቶዶሮኪ መጀመሪያ ላይ ስለ ፕላስቲክ ቀዶ ህክምና ግልጽ መረጃ ቢኖረኝ ኖሮ አላደርገውም ስትልም ጠቅሳለች።
ወጣቶች የእሷ አይነት እጣ እንዳይገጥማቸው በሚል የዩቲዩብ ቻናል ከፍታ በማስተማር ላይ ስትሆን በጥቂት ጊዜ ውስጥ ከ400 ሺህ በላይ ተከታዮችን እንዳፈራች ተናግራለች።
ወጣቶች ስለ ፕላስቲክ ቀዶ ህክምና ጉዳቶች እና ጥቅሞች በሚገባ መረጃ ካገኙ በኋላ በራሳቸው እንዲወስኑ ማድረግ ደግሞ ዋነኛ አላማዋ መሆኑን ጠቁማለች።