ቀዶ ጥገና የሚያደርጉት ጉንዳኖች
በጠንካራ ሰራተኝነታቸው የሚታወቁት ጉንዳኖች የቡድን አባላቸው ጉዳት ሲያጋጥመው የእጅ እና እግር ቀዶ ጥጋና እንደሚያደርጉ ሳይንስ አረጋግጧል
ሳይንቲስቶች ቡኒ ጉንዳን የተባሉት የጉንዳን ዝርያዎች በዚህ የተካኑ ናቸው ብለዋል
በጠንካራ ሰራተኝነታቸው የሚታወቁት ጉንዳኖች የቡድን አባላቸው ጉዳት ሲያጋጥመው የእጅ እና እግር ቀዶ ጥጋና እንደሚያደርጉ ሳይንስ አረጋግጧል
ሳይንቲስቶች ቡኒ ጉንዳን የተባሉት የጉንዳን ዝርያዎች በዚህ የተካኑ ናቸው ብለዋል
ለዘመናት በጠንካራ ሰራተኝነታቸው እና በትብራቸው የሚታወቁት ጉንዳኖች አሁን ደግሞ የቀዶ ጥገና ህክምናን እንደሚሰጡ ሳይንስ አረጋግጧል፡፡
በመኪና አደጋ እና በጦርነት እንዲሁም በተለያዩ አደጋዎች በሰው ልጆች እጅ እና እግር ላይ ጉዳት ሲደርስ ወደ ኢንፌክሽን ተቀይሮ የከፋ ጉዳት እንዳያስከትል የተለያዩ ህክምናዎች ይሰጣሉ፡፡
ጉዳት የደረሰበትን አካል ማጽዳት ፣ የአጥንት ስብራትን መጠገን ፣ መስፋት እና የከፋ ሲሆንም ቆርጦ ማስወገድ በእጅ እና እግር ላይ ጉዳት ሲያጋጥም ከሚሰጡ የህክምና አይነቶች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡
“ካምፖነተስ ፍሎሪዳነስ” በሚል ሳይንሳዊ መጠሪያ የሚታወቁት ቡኒ ጉንዳኖች የቡድን አጋራቸው እጅ እና እግር ላይ ጉዳት ባጋጠመ ጊዜ ህይወቱን ለማትረፍ ልክ እንደሰው ልጅ ሁሉ ህክምና እንደሚያደርጉለት ተነግሯል፡፡
በደቡብ ምስራቅ የአሜሪካ ክፍል በስፋት የሚገኙት 1.5 ሴንቲ ሜትር የሚረዝሙት እነኚህ ጉንዳኖች ጉዳት የደረሰበትን አካል በአፋቸው ካጸዱ በኋላ አደጋው የከፋ ከሆነ ጉዳቱ የደረሰበት እጅ ወይም እግር ከሆዳቸው ጋር በሚኖረው ርቀት ልክ ቆርጠው በመጣል የተጎጂውን ጉንዳን የመኖር እድል ለመጨመር እንደሚጥሩ ሳይንቲስቶቹ ገልጸዋል፡፡
ምርምሩን ያደረጉት የጀርመኑ ወርዝበርግ ዩኒቨርስቲ ተመራማሪ ኤሪክ ፍራንክ “አስገራሚው ነገር ጉዳት የደረሰበት አካል መቆረጥ እንዳለበት እና እንደሌለበት የሚወስኑበት መንገድ ነው፤ አንዳንዴ ቁስሉ እንዳያመረቅዝ የቆሰለውን ስፍራ ብቻ በአፋቸው ቆርጠው ሲጥሉ ሌላ ግዜ ደግሞ እጁን ወይም እግሩን ሙሉ ለሙሉ ከጉንዳኑ አካል ላይ በማስወገድ አጋራቸውን ለማትረፍ ይጥራሉ” ብለዋል፡፡
ተመራማሪው አክለውም ከሰው ልጆች ባለፈ እንስሳት በዚህ ልክ በጥንቃቄ የህክምና ስርአትን ሲተገብሩ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ሲሉ ነው የገለጹት፡፡
በላብራቶሪ ውስጥ ምርምር የተደረገባቸው ጉንዳኖች ህክምናውን ሲያደርጉ እጅ ወይም እግሩን ሙሉ ለሙሉ ማስወገድ እንደሚኖርባቸው በምን አይነት መነሻ ውሳኔ ላይ እንደሚደርሱ ባይረጋገጥም፤ ከተጎዳው አካል የሚወጣው ፈሳሽ የኢንፌክሽን ደረጃውን የሚያውቁበት መንገድ ሊሆን እንደሚችል ተመራማሪዎቹ መላምት አስቀምጠዋል፡፡
የተጎዳውን ክፍል ቆርጦ ለማስወገድ በሚያደርጉት ጥረት ሂደቱ ከ40 ደቂቃ እስከ 3ሰአት ድረስ እንደሚፈጅ የገለጹት ሳይንቲስቶቹ ህክምናው ያልተደረገላቸው ጉንዳኖች በህይወት የመተረፍ አድላቸው 40 በመቶ ሲሆን በአንጻሩ ህክምናውን ያገኙ ጉንዳኖች የመትረፍ እድል ደግሞ ከ90 እስከ 95 በመቶ ነው ብለዋል፡፡