በቲክቶክ ዳግም መነጋገሪያ የሆነው የፕላስቲክ ቀዶ ጥገና ሀኪም - “ዶክተር ኪም”
ማንነቱ አከራካሪ ሆኖ የቀጠለው “ዶክተር ኪም” እስከ 50 ሺህ ዶላር እያስከፈለ የፕላስቲክ ቀዶ ጥገና ይሰራል ተብሏል
“ዶክተር ኪም” ከሰሞኑ በቲክቶክ የለቀቀው ስራ ግን የቀደመውን ጥርጣሬ ያጎላ ሆኗል
በፕላስቲክ ቀዶ ጥገና ስራው በቲክቶክ ዝናን ያተረፈው “ዶክተር ኪም” ዳግም መነጋገሪያ ሆኗል።
የደንበኞቹን ቅድመ እና ድህረ ቀዶ ጥገና ምስል በማጋራት የሚታወቀው “ዶክተር ኪም” ከሰሞኑ እዩልኝ ብሎ ያጋራው ምስል ግን ትዝብት ውስጥ ጥሎታል።
የእጁን የድካም ፍሬ ለማሳየት “ቀድሞ እንዲህ ነበረች አሁን ግን ወዲህ ተቀይራለች” የሚል መግለጫ የሰጠው ቪዲዮ ነው ግለሰቡ በርግጥስ ፈቃድ ያለው የፕላስቲክ ቀዶ ጥገና ሀኪም ነው ወይ ያስባለው።
በምስሉ ላይ የፕላስቲክ ቀዶ ጥገና ተሰርቶለታል የተባሉት ሴቶች አሁንም ፊታቸው እንደተሸበሸበ አብጦና ቁስለቱም ሳይለቅ ይታያል።
ባለፈው አመትም ባጋራቸው ተንቀሳቃሽ ምስሎች ምክንያት ባለሙያነቱ ላይ ጥርጣሬውን አጉልተውበት የነበረው “ዶክተር ኪም” ሙሉ ስሙም ሆነ የሚኖርበት ሀገር አይታወቅም።
ሰርጂካል ታይምስ የተሰኘ ድረገጽ ግን የ”ዶክተር ኪም”ን ምስል በመጠቀም ባደረገው ፍለጋ በቲክቶክ የገነነው ግለሰብ ሙሉ ስም ኪም ጂ ሆን እንደሚሰኝ አረጋግጫለሁ ብሏል።
ደቡብ ኮሪያዊ መሆኑንና ባስቀመጠው የዋትስአፕ ስልክ ቁጥር ሲደወል ግን በቻይና ሻንጋይ አገልግሎቱን እንደሚሰጥና እስከ 50 ሺህ ዶላር ክፍያ እንደሚጠይቅ ነው ድረገጹ ያስነበበው።
የግለሰቡ ባለሙያነት በቀዶ ጥገና ሀኪሞችም ሆነ አገልግሎቱን በሚፈልጉ ሰዎች መካከል የጋለ ክርክር ቢያስከትልም አሁንም ድረስ “በዶክተር ኪም” እጅ ተዳብሰው ለስላሳ እና ያልተጨማደደ ፊት ለማግኘት ቀጠሮ የያዙ ሰዎች ቁጥር ቀላል አይደለም ተብሏል።
አንዳንዶቹም አድናቆታቸውን እየገለጹለት ሲሆን፥ አስተያየት ሰጪዎች ግን “ዶክተር ኪም” በቲክቶክ የራሱን ፊት በግልጽ እንዲያሳይ መጠየቃቸውን ኦዲቲ ሴንትራል አስነብቧል።