1443ኛው የዒድ አልፈጥር በዓል እየተከበረ ነው
በበዓሉ ላይ የጎረቤት ሀገራት የእስልምና ተቋማት ተወካዮች ተሳትፈዋል
ታላቁ የኢድ ሰላት በኢትዮጵያ በአዲስ አበባ ስታዲየም ተካሂዷል
1443ኛው የዒድ አልፈጥር በዓል እየተከበረ ነው በመላው ሀገሪቱ እየተከበረ ይገኛል።
በዓሉ በተለይም በአዲስ አበባ ስታዲየም የእስልምና የእምነት አባቶች፣ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ ከጎሮቤት አገራት የወጡ እንግዶች ፣ ዳያስፖራዎች፣ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት እና የእምነቱ ተከታዮች በተገኙበት ተከብሯል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር ኢድሪስ፤ በታላቁ የኢድ ሰላት በኢትዮጵያ ላይ ለመታደም አዲስ አበባ የገቡ የጎረቤት ሀገራት የእስልምና ተቋማት ተወካዮች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክትና ለ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
አንድነት፣ ሰላም፣ ልማት፣ ዕድገት ሁሌም ለኢትዮጽያ አስፈላጊ መሆኑን የገለጹት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር ኢድሪስ፤ "ሰላም የሚመጣው በተግባር፣ በህዝብ፣ በመንግስት ነው” ብለዋል
ይህንንም በማወቅ ወደ ሰላም፣ ወደ ልማት ልንመለስ ይገባልም ብለዋል ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር ኢድሪስ።
አክለውም የንጹሃን ደም አይፍሰስ፣ ሰዎች አይፈናቀሉ፣ አንዱ አንዱን አይዝረፍ ያሉ ሲሆን፥ ይህን ተግባር በመተው ወደሰላም እንመለስ ሲሉም መክረዋል።
ምክር ቤቱ ለሰላም መታገሉን የገለጹት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር ኢድሪስ “አንድነቱን፣ ሰላሙንና ልማቱን እውነት ያድርገው” ሲሉም መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡
ህዝበ ሙስሊሙ ሊከባበር፣ ሊፈቃቀር እና አንድነት ሊኖረው እንደሚገባ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር እድሪስ ጥሪ አቅርበዋል።