“የዘንድሮው ረመዳን በኢትዮጵያ ፍቅርና ሀገራዊ አንድነት የታየበት ሆኖ በማለፉ ከመቼም ጊዜ የተለየ ተደርጎ በታሪክ ሲታወስ ይኖራል“ - ጠ/ሚ ዐቢይ
በመልዕክቱ ወቅቱ በትዕግሥት ሰከን ብሎ ነገሮችን በጥሞና መመርመር የሚያስፈልግበት እንደሆነ ገልጸዋል
ጠቅላይ ሚኒስትር ለታላቁ የዒድ አል ፈጥር በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክትን አስተላልፈዋል
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ታላቁን የዒድ አል ፈጥር በዓል በማስመልከት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክትን አስተላለፉ፡፡
በመልዕክቱ “የዘንድሮው ረመዳን በኢትዮጵያ ፍቅርና ሀገራዊ አንድነት የታየበት ሆኖ በማለፉ ከመቼም ጊዜ የተለየ ተደርጎ በታሪክ ሲታወስ ይኖራል“ ብለዋል፡፡
“ከዒድ እስከ ዒድ” የተሰኘው ሀገራዊ ንቅናቄ ብዙዎችን ከመላው ዓለም አሰባስቦ በእናታቸው ቤት፣ በወገናቸው መሐል እንዲያሳልፉ ዕድል ፈጥሯል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከአዲስ አበባ ጀምሮ በክልል ከተሞችና በየቀየው በተዘጋጁ የጎዳና ላይ የኢፍጣር ፕሮግራሞች ወንዱ - ሴቱ፣ ሙስሊሙ - ክርስቲያኑ፣ ትንሹ - ትልቁ ኅብረትና አንድነቱን ማሳየቱን ገልጸዋል።
የቱንም ያህል የሐሳብ፣ የባህልና የወግ እንዲሁም የቋንቋና የልማድ ልዩነት ቢኖር ልዩነቶችን ተሻግሮ ወንድማማችና እኅትማማች መሆንና እርስ በእርስ መተሳሰብ እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት የእምነቱ አስተምህሮ በማሳያነት በመጠቆም።
በስልጤ ዞን በቤተክርስቲያናት እና በቤተአምልኮዎች ላይ የደረሰውን ጥቃት ጉባኤው አወገዘ
በትንሽ በትልቁ እልህና ጠበኝነትን የሚቆሰቁሱ "የሸይጣን እጆች" በበዙበት በዚህ ወቅት በትዕግሥት ሰከን ብሎ ነገሮችን በጥሞና መመርመር ከሁላችንም የሚጠበቀው ነው ብለዋል፡፡ የተመኙትን ለመጨበጥ፣ ከምንም ነገር በላይ ረጋ ብሎ ማሰብና ማሰላሰል እንደሚያስፈልጉም አስገንዝበዋል፡፡
"እንደ ሕዝብ ለሀገራችን በጥሞና እንጸልይ፣ በሚዛናዊ ምልከታ እንራመድ፣ ለመልካምነትና ደግነት ራሳችንን እናስገዛ፣ የሸይጣን እጆችን በትዕግስትና በማስተዋል በትር እንርታ" ሲሉም ጠይቀዋል።
ሀገርን መገንባት እጅግ ብርቱ ድካም የሚጠይቅ መሆኑን በማስታወስም ራሳችንን ከሌሎች አልባሌ ነገሮች ቆጥበን፣ ዕውቀትና ጉልበታችንን ከፍ ያለ ቦታ ለመድረስ እናውለው ብለዋል።
"ኢትዮጵያ፣ ገና አሁን ከጦርነት የወጣች ሀገር ናት። ከዚያ በፊት አንበጣና ኮሮና ጫና አሳርፎብን ነበር። እሱም ሳይበቃ ድርቅ ቁጥሩ ቀላል ያልሆነ ወገናችንን ክፉኛ ጎድቶታል። ብዙ ያጣነው ነገር አለና ስለጎደለብን መታገሥና በርትተን መሥራት እንጂ ተስፋ መቁረጥ የለብንም። መንግሥት የሚችለውን ሁሉ ያደረጋል። እናንተም ለሀገር ህልውና ሲሉ የተሠዉ ጀግኖችን ወደ ሕይወት መመለስ ባትችሉ በሕይወት ያሉትን መርዳት፣ ቤተሰባቸውን መደገፍ ይገባችኋል" ሲሉም አስቀምጠዋል በመልዕክታቸው።
ግጭቶችን ሃይማኖታዊ ገጽታ በማላበስ እንዲባባሱ ለማድረግ የሚሞክሩ ኃይሎችን እንደማይታገስ መንግስት አስታወቀ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በድርቁም ሆነ በግጭቶች የተሰደዱ ወገኖች ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ፣ ስራ እንዲፈጠርላቸውና ዐቅም በፈቀደ መጠን እንዲታገዙም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
እምነት ሳይለያየን ሁላችንም ተባብረን የወደቀ ወገናችንን በማንሣት ለሀገርና ለሕዝብ ያለንን ፍቅር ለዓለም እናሳይም ነው ዶ/ር ዐቢይ ያሉት ይህ ሲሆን ሰውም ፈጣሪም ደስ እንደሚሰኝ በመጠቆም።
"ከዒድ እስከ ዒድ፣ ሁላችንንም የሚመለከት የህዝብ በዓል፣ የሀገር በዓል ይሆንልናል። የዚህ በዓል በደመቀ ሁኔታ መከበር፣ የሁላችንም ድምቀት፣ የሁላችንም ክብር እንደሆነ ማወቅ ይገባናል" ሲሉም ነው መልዕክት ያስተላለፉት።