በጎንደር በተፈጠረው ችግር ወቅት የመንግሥት የፀጥታ አካላት ኃላፊነታቸውን አልተወጡም- ተቀዳሚ ሙፍቲ ሀጂ ዑመር እድሪስ
በኃላፊነት ላይ ያለ ሁሉ ስለ ሰላም ያወራል ነገር ግን ከጀርባ ሸሩንን የሚጎነጉነው እሱ ነው ብለዋል
ተቀዳሚ ሙፍቲ ሀጂ ዑመር እድሪስ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ ኃላፊነት ላይ ያሉ ሰዎች ችግሩ እልባት እንዲያገኝ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሀጂ ዑመር እድሪስ በወቅታዊ ጉዳይ መግለጫ ሰጥተዋል።
ተቀዳሚ ሙፍቲ ሀጂ ዑመር እድሪስ በመግለጫቸው “ጎንደር ላይ የተፈጠረው ጉዳይ ሄደን ባንመለከተውም ባጣም አዝነናል፤ ተበሳጭተናልም” ብለዋል።
“በጎንደር የተከሰተው ነገር በአንድ ወገን ኃይማኖታዊ ይመስላል፤ እውነታውን እዛ ሂደን አጣርተን እንድ በአንድ አልተረዳንም” ሲሉም ተናረግረዋል።
ተቀዳሚ ሙፍቲ ሀጂ ዑመር እድሪስ አክለውም፤ “የችግሩ ምንጭ ማን ነው ማንስ ጀመረው፤ ምን ያክል ሰው ተጎዳ የሚለውን አጣሪ ኮሚቴ በማዋቀር ወደ አካባቢው በመላክ እውነታውን አጣርተን እናሳውቃለን” ብለዋል።
በጎንደር በተፈጠረው ችግር የሰው ህይወት እስከሚጠፋ፣ የእምነት ቦታ እስኪወድም አንዲሁም ንብረት እስኪቃጠል ድረስ የአካባቢው አስተዳደርና የክልል መንግሥት የፀጥታ አካላት ተግባራቸውን አልተወጡም ብለዋል። “ኃላፊነት ላይ ያሉ ሰዎች ከላይ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ ይህ ጉዳይ በአስቸኳይ እልባት አግኝቶ ህዝቡ ወደ ሰላም እንዲመለሱ እንጠይቃለን” ብለዋል።
“በክልሉ ያለ ሁሉም የመንግስት ኃላፊ ከቀበሌ ጀመሮ እስከ ክልሉ አስተዳዳሪ ድረስ መጀመሪያ ችግር ሲፈጠር ማሥቆም ባለመቻላቸው ኃላፊነታቸውን አልተወጡም” ያሉ ሲሆን፤ “ይህ ችግር በአስቸኳይ እንዲወገድ እንዲደረግ እንጠይቃለን” ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
“የደረሰው አደጋ ለክርስቲያኑም ለሙስሊሙም ልክ አይደልም፤ አጥፊዎቹ በአስቸኳይ ተለይተው አስተማሪ እርምጃ ሊሰድባቸው” ይገባል ሲሉም ጠይቀዋል። ተቀዳሚ ሙፍቲ ሀጂ ዑመር እድሪስ በመግለጫቸው አክለውም፤ “ኃላፊነት ላይ ያለ ሰው ሁሉ ስለ ሰላም ያወራል ነገር ግን ከጀርባ ሆኖ ሸሩን የሚጎነጉነው፣ ተንኮል የሚሰራው፣ ደም እንዲፋሰስ የሚያደርገው እሱ ነው” ብለዋል።
“በቃላችን ሰላም ሰላም እንላለን ተግባራችን በግልባጭ ተቃራኒ ነው፤ በኃላፊነት ላይ ያሉ ወንድሞቻችን ቀበሌ፣ ወረዳ፣ ዞን፣ ክልል ምንድነው የሚጠብቀው፤ ሰላምን ለመጠበቅ እኮ ነው እዛ የተቀመጠው፤ ሰላምን የማያስጠብቅ ከሆን እዛ ኃላፊነት ላይ ምን ይሰራል” ብለዋል።
ማንኛውም ኃይማት ተገዳደሉ፣ እርስ በእርሰች ተጣሉ፣ የንጹሃንን ደም አፍሱ የሚል የለም፤ ኃይማኖት ተከባበሩ፣ ተባበሩ፣ ተመካከሩ፣ ተረዳዱ ነው የሚለው”ሲሉም አስታውቀዋል።“የኃይማኖት መሪዎች የኃይማኖት አባት እንደመሆናችን ህዝቡን ስለ ሰላም ማስተማር አለብን፤ ወደ ሰላም፣ ወደ እንደንት መጥራት አለብን” ብለዋል።
“በኃይማት አባቶች ውስጥም ከሙስሊሙም ከክርስቲያኑም ፖለቲከኞች አሉ” ያሉት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሀጂ ዑመር እድሪስ “እነዚህ አባቶች ሀገር የሚያባሉ፣ ለሸር ለተንኮል የሚቀሰቅሱ ናቸው” ብለዋል።“የኃማኖት አባት ጀርባ እና ሆድ የለውም፤ የኃይማኖት አባት ሰውር እና ገሃዱ እንድ ነው ስለዚህ ሁላችንም ትክክለኛ አባት እንሁን፤ እውነተኛ አባት ሆነን ሀገራችንን እንገንባ” ብለዋል።