ባለሙያዎቹ የኮሮና ቫይረስ መነሻ ምክንያትን ለማጥናት ነበር ወደ ዉሀን የሚሄዱት
የኮሮና ቫይረስን መነሻ ምክንያት ለማወቅ ወደ ቻይና ያቀናው የየዓለም ጤና ድርጅት የሳይንቲስቶች ቡድን የቫይረሱ መነሻ ወደ ሆነችው ዉሀን እንዳይገባ መታገዱን ተቋሙ አስታወቀ፡፡
የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ቴድሮስ አድሃኖም (ዶ/ር)፣ ሁለት ሳይንቲስቶች የኮሮና ቫይረስ ቀድሞ ወደ ተገኘበት የዉሀን ከተማ ለመሄድ ቢዘጋጁም የቻይና ባለሥልጣናት ግን ወደ ቤጂንግ እንዳገቡ መከልከላቸውን አስታውቀዋል፡፡ ለወራት ከተደረገ ድርድር በኋላ ባለሙያዎቹ ወደ ቻይና የሚያደርጉትን ጉዞ በተመለከተ ከሀገሪቱ ባለሥልጣናት ጋር በታህሣሥ ወር መግባባት ላይ ተደርሶ እንደነበር ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል፡፡
የሳይንቲስቶች ቡድን ወደ ቻይና እንዳይገቡ የመከልከላቸው ዜና እንዳበሳጫቸው ዶ/ር ቴድሮስ ገልጸዋል፡፡ ሁለት ባለሙያዎች ጉዞ እንደጀመሩ እና ሌሎቹ በተፈጠረው ችግር ምክንያት ባለቀ ሰዓት ጉዞ ማድረግ እንዳልቻሉም ነው የተናገሩት፡፡
ከቻይና ባለሥልጣናት ጋር በነበራቸው ውይይት ፣ በዉሃን ከተማ ተገኝቶ የቫይረሱን መነሻ ምክንያት የማጣራት ተልዕኮ የዓለም ጤና ድርጅትና የዓለም አቀፉ ቡድን መሆኑን ለቤጂንግ ሹሞች መግለጻቸውን ሲኤንኤን ዘገቧል፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ ይህንን ተልዕኮ ለመፈጸም ድርጅቱ እንደሚፈልግና ቤጂንግ የውስጥ ሂደቶችን ቶሎ እንደምታጠናቅቅ ያላቸውን እምነትም ገልጸዋል፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት የአስቸኳይ ጤና ፕሮግራም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ሚሼል ሪያን ፣ ከቪዛ ጋር በተያያዘ ያላለቀ ጉዳይ እንዳለና ወደ ሥፍራው ለማቅናት ጉዞ ከጀመሩት ሳይንቲስቶች አንዱ ወደ ቤቱ መመለሱን አረጋግጠዋል፡፡ ወደ ሥፍራው ለመጓዝ ተነስተው ከነበሩት አንደኛው ሳይንቲስት ግን አሁንም በስም ባልተጠቀሰች ሦስተኛ ሀገር ላይ ሆኖ ትራንዚት እየጠበቀ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት ኃላፊዎች ዓለም አቀፍ ሳይንቲስቶች የኮሮና ቫይረስ በመጀመሪያ ወደተቀሰቀሰባት ውሃን ከተማ ገብተው ፣ የቫይረሱን መነሻ እንዲያጣሩ ከቻይና ባለስልጣናት ጋር ለረዥም ጊዜ እየተነጋገሩ እንደነበር ተዘግቧል፡፡
በሌላ በኩል የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ሁአ ቹንይንግ ከዶ/ር ቴድሮስ አንድ ቀን ቀደም ብለው ሰኞ በሰጡት አስተያየት ፣ የዓለም ጤና ድርጅት ባለሙያዎች ቡድን ወደ ቻይና ቢመጣ እንደሚቀበሉ መግለጻቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ከ 100 በላይ ሀገራት የቫይረሱ መነሻ እንዲጣራ በጠየቁት መሰረት ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ላይ ፣ የዓለም ጤና ድርጅት ምርመራ እንዲጀመር መስማማቱ ይታወሳል፡፡ ዶ/ር ሪያን ሎጀስቲክስ እና የቢሮክራሲ ጉዳዮች በአስቸኳይ ተፈተው ሳይንቲስቶቹ ወደ ቻይና እንደሚገቡ ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡
አሜሪካና አውስትራሊያ ቻይና ቫይረሱን የተቆጣጠረችበት መንገድ ትክክል አይደለም በሚል ሲቃወሙ ነበር፡፡ ተሰናባቹ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በተደጋጋሚ ቻይናን ሲወቅሱ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን የኮሮና ቫይረስንም የቻይና ቫይረስ ሲሉት ነበር፡፡
አሜሪካ የዓለም ጤና ድርጅት በቻይና እየሰራ ያለው ሥራ ግልጽ ይደረግ የሚል ጥያቄ መጠየቋም የሚታወስ ነው፡፡