ኮሮና ቢያንስ የ115 ሺ ጤና ባለሙያዎችን ህይወት እንደቀጠፈ የዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ
ጤናማ፣ ደህንነቱን የሚፈልግ ማንኛውም ሀገር የጤና ባለሙያዎች ላይ ኢንቨስት ማድረግ እና መንከባከብ አለበት
በርካታ የዘርፉ ባለሙያዎች የሌሎች ሰዎችን ህይወት ለማዳን ሲሉ ህይወታቸውን አጥተዋል- ዶ/ር ቴድሮስ
ኮቪድ 19 ወረርሽኝ በዓለማችን ላይ ከተከሰተ ጀምሮ እስካሁን ቢያንስ 115 ሺህ የጤና ባለሙያዎች ህይወት ማለፉን የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ተናገሩ።
ዶ/ር ቴድሮስ በዛሬው እለት እንዳስታወቁት፤ በዓለም ዙሪያ በርካታ የጤናው ዘርፍ ባለሙያዎች የሌሎች ሰዎችን ህይወት ለማዳን ሲሉ ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡
እስካሁን ቢያንስ የ115 ሺህ የጤና ባለሙያዎች ህይወት በወረርሽኙ ሳቢያ ማለፉን ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ በርካቶች ደግሞ በቫይረሱ ተይዘዋል ሲሉ መናገራቸውንም ሲ.ጂ.ቲ.ኤን ዘግቧል።
ሲ.ጂ.ቲ.ኤን በ74ኛው የዓለም ጤና ጉባኤ ላይ “የጤና ባለሙያዎች ላፉት 18 ወራት በሞት እና በህይወት መካከል ሆነው ሲሰሩ ነበር” ሲሉ ንግግር ያደረጉት ዶ/ር ቴድሮስ እጅግ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎችን ህይወት ታድገዋል ስለማለታቸውም ነው የዘገበው፡፡
ጤናማ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ እና ብሩህ ተስፋን የሚፈልግ ማንኛውም ሀገር ነገ ዛሬ ሳይል የጤና ባለሙያዎች ላይ መስራት እና መንከባከብ ይገባዋል ሲሉም መልእክት አስተላልፈዋል።
ዶ/ር ቴድሮስ አክለውም “ዛሬ ጠዋት 74ኛ ጉባዔ ከተጀመረ አንስቶ ቢያንስ 1000 ሰዎች በኮቪድ 19 ሳቢያ ህይወታቸውን አጥተዋል” ሲሉም ተናግረዋል።