ኮቪድ 19 ሲጋራ ማጨስን ማቆም ለሚፈልጉ ተጨማሪ ምክንያት ነው- የዓለም ጤና ድርጅት
ሲጋራ አጫሾች በኮቪድ 19 መሞት እድላቸው ከማያጨሱት ጋር ሲነጻጸር በ50 በመቶ ከፍ ያለ ነው
የዓለም “ከትምባሆ ነፃ ቀን” ዛሬ በዓለም ለ34ኛ በኢትዮጵያ ለ29ኛ ጊዜ እየተከበረ ነው
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሲጋራ ማጨስን ማቆም ለሚፈልጉ አጫሾች ተጨማሪ ምክንያት መሆኑን የዓለም ጤና ድርጅት ገለፀ።
የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም በዛሬው እለት ለ34ኛ ጊዜ የሚከበረውን የዓለም “ከትምባሆ ነፃ ቀን” አስመልክቶ ባስተላለፉት መልእክት፣ ሲጋራ የሚያጨሱ ሰዎች ለኮቪድ 19 የመጋለጥ እድላቸው በጣም ከፍተኛ ነው ብለዋል።
ሲጋራ አጫሾች በኮቪድ 19 ሳቢያ የመሞት እድላቸው ከማያጨሱት ጋር ሲነጻጸር በ50 በመቶ ከፍ ያለ መሆኑንም ነው ዶክተር ቴድሮስ ያስተወቁት።
ስለዚህ በዚህ ወቅት ሲጋራ ማጨስን ማቆም ለኮቭድ 19 የመጋለጥ እና በቫየረሱ ሳቢያ የሚደርስ ሞትን ለመከላከል ዋነኛው አማራጭ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
ሲጋራ ማጨስን በማቆም ከኮቪድ 19 በተጨማሪ ለካንሰር፣ ለልብ ህመም እና ለመተንፈሻ አካል በሽታዎች የመጋለጥ እድልን መቀነስ እንደሚቻልም ነው ያስታወቁት።
የዓለም ትምባሆ የማይጨስበት ቀን በኢትዮጵያም ለ29ኛ ጊዜ "ትምባሆ ያጨሳሉ? እንግዲያውስ ለማቆም ቆራጥ ይሁኑ” በሚል መሪ ቃል እየተከበረ ይገኛል።
የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ ባስተላለፉት መልእክት ፣ ቀኑ ትንባሆ እያደረሰ ያለውን ጉዳት ለህብረተሰቡ
ለማስገንዘብና ከትንባሆ ነፃ የሆነች ዓለምን ለመፍጠር ታስቦ እንደሚከበር ተናግረዋል
ከኮቪድ 19 ጋር በተያያዘ ትምባሆ አጫሾች ለፅኑ ህመምና ለሞት ይበልጥ ተጋላጭ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።
በዓለም 8 ሚሊዮን ሰዎች በትምባሆ ምክንያት በየዓመቱ ህይወታቸው እንደሚያልፍ መረጃዎች ያመለክታሉ።