ልዩልዩ
15ኛው የአል ዳፍራ የግመሎች የቁንጅና ውድድር ዛሬ በአቡዳቢ ይጀመራል
የውድድሩ መካሄድ ዩኤኢ ሃገር በቀል እሴቶቿን ጠብቆ ከማቆየትም በላይ ለማስተዋወቅ እንደሚያግዛት ተገልጿል
ውድድሩ ለቀጣዮቹ አስር ቀናት የሚካሄድ ሲሆን 313 ግመሎች ይሳተፉበታል ተብሏል
15ኛው የአል ዳፍራ የግመሎች የቁንጅና ውድድር ዛሬ በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች (ዩኤኢ) ርዕሰ መዲና አቡዳቢ ይጀመራል፡፡
በአቡዳቢው ልዑል መሃመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን የበላይ ጠባቂነት በየዓመቱ የሚካሄዴው ይህ የግመሎች የቁንጅና ውድድር ዛሬ በአቡ ዳቢ አል ዳፍራ ክልል በመዲናት ይጀመራል ተብሏል፡፡
ለቀጣዮቹ 10 ቀናት እንደሚዘልቅ የተነገረለት ውድድሩ አቡዳቢ የዩኤኢን ሃገር በቀል እሴቶች ጠብቆ ከማቆየትና ለማሳደግ ከመስራትም በላይ ለመላው ዓለም ለማስተዋወቅ የምታደርገውን አስተዋጽዖ የሚያሳይ ነው ተብሏል፡፡
ሃገር በቀል እሴቶችን በተለይም የግመሎችን ዝርያ ሳይበረዝ ጠብቆ ለማቆየት የተያዘውን ሃገራዊ ውጥን ከግምት ውስጥ በማስገባት የሚካሄድ መሆኑም ነው የተገለጸው፡፡
ለእንዲህ ዐይነት እሴቶች ዋጋ የሚሰጡ የውጭ ሃገራት ጎብኚዎችንና አጥኚዎችን ቀልብ ለመሳብ ያስችላልም ተብሏል፡፡
የተለያዩ ዝርያዎች ያሏቸው 313 ግመሎች ይሳተፉበታል በተባለለት በዚህ ውድድር ሽልማቶች መዘጋጀታቸውንም የውድድሩ አዘጋጆች አስታውቀዋል፡፡