ጋለሪው ውስጥ ስዕል፣ ፈርኒቸር፣ የሸክላ ውጤቶች፣ ጨርቃ ጨርቅ፣ የዕደ ጥበብ፣ መስቀሎችና ሌሎችም አሉ
ወ/ሮ ሰላማዊት አለነ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሸራተን አዲስ ሆቴል ጎን የሚገኘው እና በ1983 ዓ.ም የተቋቋመው ሴንት ጆርጅ ጋለሪ ስራ አስኪያጅ እና ባለቤት ናቸው።
ይህን ጋለሪ በእህታቸው ወ/ሮ ሳባ አለነ አማካኝነት እንደተጀመረ እና ወ/ሮ ሰላማዊትም ከስምንት ዓመታት በኋላ ወደ ጋለሪው መቀላቀላቸውን ለአል ዐይን አማርኛ ገልጸዋል።
የዚህ ጋለሪ ዋነኛ ዓላማ የሥነ ጥበብ ማዕከል ማድረግ መሆኑን የሚገልጹት ወ/ሮ ሰላማዊት “መሬቱን ለኔ ግድግዳውን ለሰዓሊያን” በሚል መሪ ሃሳብ በወ/ሮ ሳባ አለነ የተጀመረው ይህነ ጋለሪ በአዲስ አበባ ከተማ ባህል፣ ኪነጥበባት ቢሮ ዕውቅና እንዳለው ተገልጿል።
ከወጣት እስከ አንጋፋ ሰዓሊያን የጥበብ ውጤቶቻቸውን ለሴንት ጆርጅ ጋለሪ እንደሚያቀርቡ የገለጹት ስራ አስኪያጇ የ43 ሰዓሊያን የሥራ ውጤቶች በጋለሪው ይገኛሉ ብለዋል።
በጋለሪው ውስጥ ከሞላ ጎደል የኢትዮጵያን ጥበብ የሚያሳዩ ነገሮች እንዳሉ የተገለጸ ሲሆን ጋለሪው ስድስት ክፍሎች አሉት።
ይህ ቤት በአድዋ ጦርነት ወቅት የዘመቱት እና ብዙ ታሪክ ያላቸው የደጃዝማች ሊጋባ ጣሰው እንደሆነ የገለጹት ወ/ሮ ሰላማዊት፤ “የሸራተን ማስፋፊያ” በሚል ከዘጠኝ ዓመታት በፊት ሊፈርስ እንደነበር ለአል ዐይን አማርኛ ገልጸዋል።
በወቅቱ ከአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ እና ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ቅርሱን ከመፍረስ ማዳኑ መቻሉን ስራ አስኪያጇ ገልጸዋል።
ወ/ሮ ሰላማዊት ከሸራተን አዲስ ጎን የሚገኘው የሴንት ጆርጅ ጋለሪ ያለበት ቤት በአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ተመዝግቧል ብለዋል። ሴንት ጆርጅ ጋለሪ ሸራተን ጎን ከሚገኘው በተጨማሪም ጎላ ፓርክ ውስጥ ሌላ ጋለሪ እንዳለው ተናግረዋል።
የኮሮና ቫይረስ ከመጣ በኋላ የጎብኝዎች ቁጥር መቀነሱን ገልጸው በዚህ ጋለሪ ውስጥ ስዕል፣ ፈርኒቸር፣ የሸክላ ውጤቶች፣ ጨርቃ ጨርቅ፣ የዕደ ጥበብ፣ መስቀሎች እና ሌሎችም አሉ።
ወደ ጋለሪው መጥቶ ለመጎብኘት የሚጠየቅ ክፍያ እንደሌለ ያነሱት ስራ አስኪያጇ ይህ የተደረገውም የጥበብ አድናቂዎች ጎብኝተው የሚሄዱና የሚገዙ ሰዎችን እንዲበረታቱ ነው ብለዋል።
ይህንን ጋለሪ ወደፊት ሙዚየም ለማድረግ መታቀዱን ወ/ሮ ሰላማዊት ተናግረዋል።