የብሪክስ ሀገራት ዓመታዊ የመሪዎች ጉባኤ ነገ በደቡብ አፍሪካ ይጀመራል
የቻይናው ፕሬዝዳንት ብሪክስ የቡድን ሰባት ሀገራትን የሚፎካከር እንዲሆን ይፈልጋሉ ተብሏል
በጉባኤው ለመካፈል የቻይና እና ብራዚል ፕሬዝዳንቶችን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት መሪዎች ጆሀንስበርግ በመግባት ላይ ናቸው
የብሪክስ ሀገራት ዓመታዊ የመሪዎች ጉባኤ ነገ በደቡብ አፍሪካ ይጀመራል።
በብራዚል፣ ሩሲያ፣ ሕንድ፣ ቻይና እና ደቡብ አፍሪካ የተመሰረተው ብሪክስ በየዓመቱ የመሪዎች ጉባኤውን በመስራቾቹ ሀገራት ከተሞች ያደርጋል።
የዘንድሮው የብሪክስ መሪዎች ዓመታዊ ጉባኤን የማስተናገድ ተራው የደቡብ አፍሪካ ሲሆን ይህ ጉባኤ ነገ በጆሀንስበርግ ከተማ እንደሚካሄድ ተገልጿል።
ይህ የአምስት ሀገራት ስብስብ ለዓለማችን አዲስ ስርዓት ማበጀት ዋነኛ ዓላማው መሆኑን ካሳወቀ በኋላ የብዙዎችን ትኩረት ስቧል።
በተለይም ቻይና እና ሩሲያ በአሜሪካ እና አውሮፓዊያን እየተተገበረ ያለው ስርዓት ፍትሀዊ አይደለም፣ አለማችን አማራጭ የንግድ እና ዲፕሎማሲ ስርዓት ያስፈልጋታል በሚል የያዙትን አቋም ሀገራት እየደገፉት ይገኛሉ ተብሏል።
በሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት መጀመር ምክንያት በሞስኮ ላይ የተጣሉት ማዕቀቦች ሀገራት በዶላር ላይ የተመሰረተ የመጠባበቂያ ገንዘብ ክምችት እና ንግዳቸውን በሌሎች አማራጮችም የመደገፍ ፍላጎታቸው መጨመሩ ለብሪክስ መጠናከር ምክንያት ሆኗል፡፡
ከዓለም ህዝብ ውስጥ 42 በመቶ ድርሻ ያለው ብሪክስ እውነታዎች
በዘንድሮው የብሪክስ ዓመታዊ ጉባኤ ላይ ለመካፈል የቻይና ፕሬዝዳንት ሺ ፒንግ፣ የብራዚሉ ፕሬዝዳንት ሉላ ዳ ሲልቫ ጆሀንሰበርግ መድረሳቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።
በተጨማሪም የኢራኑ ፕሬዝዳንት ሬሲ፣ የሕንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ እና የሌሎች ሀገራት መሪዎች ወደ ደቡብ አፍሪካ በመጓዝ ላይ እንደሆኑም ተጠቅሷል።
ሩሲያ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ሰርጊ ላቭሮቭ ትወከላለች የተባለ ሲሆን ፕሬዚዳንት ፑቲን ጉባኤውን በበይነ መረብ ይከታተላሉም ተብሏል።
ከወራት በፊት ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ40 በላይ የዓለማችን ሀገራት ብሪክስን ለመቀላቀል ጥያቄ ማቅረባቸው ሲገለጽ ሳውዲ አረቢያ፣ ኢራን፣ የተባበሩት አረብ ኢምሬት እና ዋነኞቹ ናቸው።ም