40 የሚሆኑ ሀገራት ብሪክስን ለመቀላቀል ፍላጎት አሳይተዋል
የብሪክስ ጉባኤ በሚቀጥለው ሳምንት በደቡብ አፍሪካ እንደሚካሄድ ተገለጸ።
የዓለምን አንድ ሦስተኛ ምጣኔ-ሀብት የያዙት የብሪክስ አባል ሀገራት ምዕራባዊያንን ለመገዳደር ወደ የጅኦ ፓለቲካ ኃይል ለመቀየር ይወያያሉ።
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በእስር ማዘዣ ምክንያት በሚቀጥለው ሳምንት በደቡብ አፍሪካ በሚካሄደው ጉባኤ እንደማይሳተፉ ታውቋል።
በጉባኤው የብራዚል፣ ህንድ፣ ቻይና እና ደቡብ አፍሪካ መሪዎች የሚታደሙ ሲሆን፤ ህብረቱን ማስፋፋት ላይ አለመግባባት ተፈጥሯል።
ሀገራቱ ለውይይት ያቀዷቸው ጉዳዮችን በተመለከተ ጥቂት ዝርዝሮች የወጡ ቢሆንም፤ 40 የሚጠጉ ሀገራት ለመቀላቀል ፍላጎት በማሳየታቸው የማስፋፊያ አጀንዳ ትልቅ ጉዳይ እንደሚሆን ይጠበቃል።
የብሪክስን ህብረት ለመቀላቀል ማመልከቻ ካስገቡት ውስጥ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሳዑዲ አረቢያ፣ አርጀንቲና እና ግብጽ ይገኙበታል።
ቻይና ከአሜሪካ ጋር ባላት ፍጥጫ የጂኦ ፖለቲካዊ ተጽዕኖን ለማስፋት የብሪክስ አባላትን በፍጥነት ማስፋፋት የፈለገች ሲሆን፤ ብራዚል ደግሞ ማስፋፋትን እየተቃወመች ነው።
በ15ኛው የመሪዎች ጉባኤ መሪ ሃሳብ "ብሪክስ እና አፍሪካ" ሲሆን፤ ህብረቱ በአለም ኃያላን ሀገራት መካከል የውድድር መድረክ እየሆነ ከመጣው አህጉር ጋር ያለው ግንኙነት እንዲጠነክር አጽንኦት ሰጥቷል።